ከህወሓት ጋር ያለውን ችግር በየትኛውም የሰላም አማራጭ ለመፍታት መስማማቱን ብልጽግና አስታወቀ
አንደኛ ድርጅታዊ ጉባዔውን በማድረግ ላይ ያለው ፓርቲው በ5 አጀንዳዎች ላይ እንደሚወያይ ገልጿል
የትግራይ ህዝብ በህወሓት ምክንያት ችግር ላይ ወድቋል ያለው ፓርቲው ችግሩን ለመፍታት አሉ የተባሉ የሰላም አማራጮችን በሙሉ እንደሚጠቀም አስታውቋል
የትኛውንም የሰላም አማራጭ ተጠቅሞ ከህወሓት ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት መስማማቱን ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ፡፡
አንደኛ ድርጅታዊ ጉባዔን በማካሄድ ላይ ያለው ፓርቲው የትግራይ ህዝብ በህወሓት ጸብ አጫሪ ድርጊት ምክንያት ያልተገባ ዋጋ እየከፈለ ነው ብሏል፡፡
የትግራይ ህዝብ ጉዳት የሌላውም ኢትዮጵያዊ ጉዳት ነው ሲሉ የድርጅታዊ ጉባዔውን የመጀመሪያ ቀን ውሎ የተመለከተ መግለጫን የሰጡት የፓርቲው የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሀላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)ህዝቡ እያጋጠመው ያለውን ችግር ለመቅረፍ የሰላም አማራጮችን ተጠቅሞ መስራት እንደሚጠበቅ ተስማምተናል ብለዋል፡፡
የብልጽግና ዓላማ ጠንካራ ፓርቲ በመሆን በእሱ የሚከወን ጠንካራ ሀገረ መንግስት መመስረት ነው- ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ
ህወሓት እያደረገው ካለው ትንኮሳና ዳግም ወረራ አንጻር በተለይም የሃገርን ሉዓላዊነትና ክብርን ለመቀልበስ ለመጉዳት የነበረው ፍላጎት የተቀለበሰ ቢሆንም በድጋሚ የመውረር ፍላጎቱ ዜሮ ሆኗል ለማለት አይቻልም ያሉት ኃላፊው ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጅት ማድረግና ራስን ማጠናከር ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይህን በማድረግ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር እንዲሁም ህልውና ዳግም አደጋ ላይ የሚጥል ነገር በሚያጋጥምበት ጊዜ አስፈላጊው እርምጃ መወሰድ እንዳለበትም ነው የገለጹት፡፡
የብልጽግና አመራርና አባላትም ይህን በአንክሮ እንዲከታተሉና ንቁ ሆኖ ለመጠበቅ የሚያስችል ዝግጅት እንዲያደርጉ ስምምነት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል ዶ/ር ቢቂላ፡፡
ዛሬ በድርጅቱ ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት መሪነት የኢንስፔክሽን እና የማዕከላዊ ኮሚቴ ሪፖርቶች ላይ ተወያይቶ ያጸደቀው ብልጽግና በሌሎች የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረሱም ተገልጿል፡፡
እስከ ነገ እሁድ መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓመት በሚዘልቀው ጉባዔው የማዕከላዊ እና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን መምረጥን ጨምሮ የአመራር ሹም ሽር እንደሚያደርግም ይጠበቃል፡