የፌስቡክ "ለካምብሪጅ አናሊቲካ ቅሌት" 725 ሚሊዮን ዶላር ሊከፍል ነው
ፌስቡክ በፈረንጆቹ 2018 ለብሪታኒያው ድርጅት 87 ሚሊዮን የሚደርሱ ተጠቃሚዎችን የግል መረጃ እንዲያገኝ ፈቅዷል በሚል ክስ ቀርቦበታል
ፌስቡክን የሚያስተዳድረው ሜታ ኩባንያ በስምምነቱ ጥፋተኝነቱን አለመቀበሉ ተነግሯል
የፌስቡክ ባለቤት ሜታ ኩባንያ ካምብሪጅ አናሊቲካን ጨምሮ የሶስተኛ ወገን የተጠቃሚዎችን ግላዊ መረጃ እንዲያገኙ ፈቅዷል በሚል የቀረበበትን ክስ ለመፍታት 725 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማምቷል።
ሐሙስ በፍርድ ቤት የተገለጸው ይህ ስምምነት በፈረንጆቹ 2018 ፌስቡክ የብሪታኒያውን የፖለቲካ አማካሪ ድርጅት ካምብሪጅ አናሊቲካ እስከ 87 ሚሊዮን የሚደርሱ ተጠቃሚዎችን መረጃ እንዲያገኝ ፈቅዶ የነበረውን የረዥም ጊዜ ክስ ይፈታል ነው የተባለው።
የከሳሾቹ ጠበቆች የታቀደውን ስምምነት በአሜሪካ ግላዊነት ክስ ውስጥ የተገኘው ትልቁ ካሳ እና ሜታ ኩባንያ ክስ ለመፍታት የከፈለውን ከፍተኛ ገንዘብ ብለውታል።
የከሳሾቹ መሪ ጠበቆች ዴሬክ ሎዘር እና ሌስሊ ዌቨር በጋራ ባወጡት መግለጫ "ይህ ታሪካዊ የካሳ ስምምነት በዚህ ውስብስብ እና አዲስ የግላዊነት ጉዳይ ላይ ትርጉም ያለውና እፎይታ የሚሰጥ ነው" ብለዋል።
ሆኖም ሜታ ኩባንያ በስምምነቱ ጥፋተኝነቱን አለመቀበሉን ሮይተርስ ዘግቧል።
ኩባንያው ባወጣው መግለጫ ስምምነቱን “የእኛን ማህበረሰብ እና የባለአክሲዮኖችን ጥቅም የሚጠብቅ ነው” ብሏል።
"ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የግላዊነት አቀራረባችንን አሻሽለነዋል እና አጠቃላይ የግላዊነት መርሃ-ግብርን ተግባራዊ አድርገናል" ብሏል ሜታ።
ካምብሪጅ አናሊቲካ በፈረንጆቹ 2016 ለዶናልድ ትራምፕ የተሳካ የፕሬዝዳንት ዘመቻ የሰራ አማካሪ ሲሆን፤ የግል መረጃዎችን በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ የፌስቡክ አካውንቶች ላይ ኢላማ ስለማድረጉ ተነግሯል።