የፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ 11 ሺ ሰራተኞቹን አሰናበተ
ከ87 ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉት ኩባንያው 13 በመቶ ሰራተኞችን ለመቀነስ ተገድጃለሁ ብሏል
የሜታ ዋና ስራ አስፈፃሚ ማርክ ዙከርበርግ "በገጠመን ከባድ ችግር ምክንያት ለቀነስናችሁ ሰራተኞቻችን ይቅርታ እጠይቃለሁ" ብሏል
የፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ 11 ሺ ሰራተኞቹን ማሰናበቱ ተነገረ።
ከ87 ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉት ኩባንያው የጠበቅኩት እድገት ባለመሳካቱ ነው እርምጃውን የወሰድኩት ብሏል።
ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ሜታ ከጠቅላላ ሰራተኞቼ 13 በመቶውን ለመቀነስ ቀንሷል።
የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ማርክ ዙከርበርግ "በገጠመን ከባድ ችግር ምክንያት ለቀነስናችሁ ሰራተኞቻችን ይቅርታ እጠይቃለሁ" የሚል መግለጫ አውጥቷል።
በታሪካችን ፈታኝ ወቅት ላይ ያሳለፍነው ውሳኔ ለሁሉም ከባድ መሆኑን አውቃለሁ ያለው የፌስቡክ መስራች ዙከርበርግ፤ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የተመዘገበውን ገቢ ተንተርሰን የወጠነው የረጅም ጊዜ እቅድ ዋጋ አስከፍሎናል ብለዋል።
የፍላጎት እና ግኝቱ አራምባ እና ቆቦ ሆኖ መገኘት ለሰራተኞቹ መቀነስ ምክንያት መሆኑንም አብራርተዋል።
ለዚህም ከመሰል ተቋማት የገጠማቸው ፉክክር ብርቱ መሆኑን አንዱ ምክንያት አድርገው ጠቅሰውታል።
ለኩባንያው ገቢ ማሽቆልቆልም ሃላፊነቱን እንደሚወስዱ ነው የጠቆሙት።
ፌስቡክ ፤ ኢንስታግራም እና ዋትሰአፕን አካቶ የእናት ኩባንያው ስያሜ ሜታ መሆኑን ሲገልፅ በርካቶች ስያሜው የሚያሳጣው ቀላል እንደማይሆን ሲገልፁ ነበር።
ከስያሜው ባሻገር እንደ ቲክቶክ ያሉ አጫጭር ምስሎችን ማጋሪያ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ተፅዕኖ ማየል ለግዙፉ ትስስር ገፅ ፈተና መሆናቸው አልቀረም።
የአጫጭር መረጃዎች መለዋወጫው ትዊተርም መሰል ችግር ገጥሞት ከሰሞኑ ከ3 ሺ በላይ ሰራተኞቹን መቀነሱ ይታወሳል።