የፌስቡክ ማስጠንቀቂያ ምርቶቻቸውን በፌስቡክና ኢንስታግራም በሚያስተዋውቁ ተጠቃሚዎች ድንጋጤ ፈጥሯል
ፌስቡክን የሚያስተዳድረው ሜታ ኩባንያ፡ የፌስቡክን እና ኢንስታግራም በመላው አውሮፓ ሊዘጋ እንደሚችል አስጠነቀቀ።
ኩባንያው የማህበራዊ ትስስር ገጾቹን ልዘጋ እችላለሁ ሲል ያስጠነቀቀበት ዋና ምክንያትም “የአውሮፓ የመረጃ ህጎች (Data regulations) መሆኑንም አስታውቋል።
ኩባንያው ህጎቹ ከአውሮፓ የሚያገኛቸው የተጠቃሚዎቹን መረጃዎች በአሜሪካው ሰረቨሩ እንዳያከማች የሚከለክሉ በመሆናቸው ነው” ሲል ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
"በምንሰራባቸው ሀገራት እና አከባቢዎች መካከል መረጃ ማስተላለፍ ካልቻልን ወይም በምርቶቻችን እና አገልግሎቶቻችን መካከል መረጃን ላለማጋራት ከተገደድን ፤ በአገልግሎታችንን ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል” ብሏል ሜታ ባወጣው መግለጫ።
ሜታ የተጠቃሚዎችን መረጃ ማወቅ ሲኖርበት አለማወቁ በኩባንያው ላይ ትልቅ ችግር እንደሚፈጥርም ነው የተገለፀው።
ሜታ ንግዱን እና ማስታወቂያ ሲያስተዋዉቅ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጾች ተጠቃሚዎችን መረጃን ማእከል አድርጎ እንደሆነ ይታወቃል።
ግዙፉን የፌስቡክ ማህበራዊ አውታረ መረብን የሚያስተዳድረው የሜታ ኩባንያ እንደፈረንጆቹ በ2022 አዳዲስ ስምምነቶች ላይ ሊደርስ እንደሚችልም ግልጽ አድርጓል።
ሜታ ይህን ማድረግ ካልቻለ ፌስቡክ እና ኢንስታግራምን ጨምሮ በርካታ ጠቃሚ ምርቶቹን እና አገልግሎቶቹን በአውሮፓ ለማቅረብ እንደማይችልም አስገንዝቧል።
የሜታ መስጠንቀቅያ በበጎ ጎኑ የሚወስዱት እንዳሉ ሁሉ፤ በትናንሽ የንግድ እንቅስቃሴዎች የተሳመሩ እና ምርቶቻቸውን በፌስቡክ እና ኢንስታግራም ለሚያስተዋውቁ ተጠቃሚዎች ግን አስደጋጭ ዜና መሆኑ እየተገለጸ ነው።