ፌስቡክ ኩባንያ የዶናልድ ትራምፕን አካውንት ላገደበት 25 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል ተስማማ
ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ውጤትን በሀይል ለማስቀየር ሞክረዋል በሚል ነበር የፌስቡክ አካውንታቸው የታገደው
ትራምፕ ከሜታ ኩባንያ የሚያገኙትን ገንዘብ ቤተ መጽሀፍት ለመገንባት ያውሉታል ተብሏል
ፌስቡክ ኩባንያ የዶናልድ ትራምፕን አካውንት ላገደበት 25 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል ተስማማ።
ከአምስት ዓመት በፊት በተካሄደ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በስልጣን ላይ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ በሌላኛው የምርጫ ተፎካካሪ መሸነፋቸው ይታወሳል።
በዚህ ጊዜ ነበር ፌስቡክ ዶናልድ ትራምፕ የምርጫውን ውጤት በሀይል ለማስቀየር በሚል አለመረጋጋት እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ ይዘቶችን በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አጋርተዋል በሚል እገዳ ጥሎባቸው ነበር።
ዶናልድ ትራምፕ የፌስቡክ እገዳ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነትን የሚገድብ ነው ብለው ተቃውመውም ነበር።
ይህን ተከትሎም ትራምፕ በሜታ ኩባንያ ላይ ክስ መስርተው የህግ ክርክር ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
ሜታ ኩባንያ በዶናልድ ትራምፕ የተመሰረተበትን ክስ በድርድር ለማቋረጥ መስማማቱን ዎልስትሪት ጆርናል ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ የፌስቡክ እናት የሆነው ሜታ ኩባንያ ለዶናልድ ትራምፕ የ25 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል ተስማምቷል።
ዶናልድ ትራምፕም ከሜታ ኩባንያ ከሚያገኙት የካሳ ክፍያ ውስጥ 22 ሚሊዮን ዶላሩን ቤተ መጽሀፍት እንደሚያስገነቡበት ሲገለጽ ቀሪው ደግሞ ለህግ አገልግሎት እንደሚከፍሉት ተገልጿል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ዳግም ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት የተመለሱት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስሜን አጥፍተዋል ባሏቸው ሚዲያዎች እና ኩባንያዎች ላይ የመሰረቷቸውን ክሶች አሸንፈዋል።
ከሁለት ወር በፊት ኤቢሲ የተሰኘው ሚዲያ 15 ሚሊዮን ዶላር ለዶናልድ ትራምፕ ካሳ ለመክፈል መስማማቱ ይታወሳል።