ቲክቶከሮች ወደ ፌስቡክ እንዲገቡ የ5 ሺህ ዶላር ጉርሻ ቀረበላቸው
የፌስቡክ እና ኢንስታግራም እናት ኩባንያ ሜታ ተጽዕኖ ፈጣሪ ቲክቶከሮች እንዲቀላቀሉት ጥሪ አቅርቧል
ኩባንያው ከ5 ሺህ ዶላር በተጨማሪም የሰማያዊ ባጅ እና ሌሎች አገልግሎቶችንም እሰጣለሁ ብሏል
ቲክቶከሮች ወደ ፌስቡክ እንዲገቡ የ5 ሺህ ዶላር ጉርሻ ቀረበላቸው፡፡
በማርክ ዙከርበርግ የተመሰረተው ሜታ ኩባንያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ቲክቶከሮች ፌስቡክ እና ኢንስታግራምን እንዲቀላቀሉ ጉርሻ አዘጋጅቷል፡፡
ፌስቡክ እና ኢንስታግራምን ለሚቀላቀሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ቲክቶከሮች የ5 ሺህ ዶላር ጉርሻ የተዘጋጀላቸው ሲሆን ለዚህም የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርቧል፡፡
ፌስቡክን የተቀላቀሉ ቲክቶከሮች በወር ቢያንስ 20 ከዚህ በፊት የትኛውም ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያልተጋራ እና አዲስ ይዘቶችን ለተከታዮቻቸው ማጋራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የ5 ሺህ ዶላር ክፍያው የሚፈጸመው የቲክቶከሮቹ የሶስት ወራት እንቅስቃሴ ከታየ በኋላ ነውም ተብሏል፡፡
እንዲሁም ፌስቡክን እና ኢንስታግራምን መቀላቀል የሚችሉት አዲስ አካውንት በመክፈት እንጂ ከዚህ በፊት የነበራቸውን መቀጠል እንደማይችሉም ተገልጿል፡፡
በአሜሪካ ለሚገኙ ቲክቶከሮች ብቻ የቀረበው ይህ እድል መተግበሪያዎቹን የሚቀላቀሉ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ከ5 ሺህ ዶላር በተጨማሪ ሰማያዊ ባጅን ጨምሮ ሌሎችን አገልግሎቶችን በነጻ እንደሚያገኙም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ቲክቶክ ለአሜሪካ ብሔራዊ የደህንነት ስጋት ምንጭ ነው በሚል በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳድር እንዲሸጥ አልያም እንዲዘጋ ውሳኔ ተላልፎበት ነበር፡፡
ለአንድ ቀን ተዘግቶ የነበረው ቲክቶክ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ከዚህ በፊት ተወስኖበት የነበረውን ውሳኔ ለተጨማሪ 75 ቀናት ተራዝሞለታል፡፡
ቲክቶክ ለአሜሪካዊያን ሙሉ ለሙሉ አልያም በከፊል እንዲሸጥ በሚል የተፈቀደለትን ጊዜ በሚገባ ካላጠናቀቀ እስከወዲያኛው በአሜሪካ ሊዘጋ ይችላል ተብሏል፡፡