ዶናልድ ትራምፕ በፌስቡክና ኢንስታግራም ብቻ 60 ሚልዮን ተከታይ ነበራቸው
የአሜሪካ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፌስቡክ ገፅ ታግዶ ሊቆይ እንደሚችል የፌስቡክ ኩባንያ ገለጸ፡፡
ኩባንያው ይህን ያለው በቀድሞ ፕሬዝዳንት ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ከማኅበራዊ አውታረመረብ ፍርድ ቤት የቁጥጥር ቦርድ የተነሳለትን ጥያቄ አዘል ትችት ተከትሎ ነው፡፡የቁጥጥር ቦርዱ ፌስቡክ በዶናልድ ትራምፕ ላይ ላልታወቀ ጊዜ እገዳ መጣሉ ከመጀመርያውኑ ትክክል አይደለምም የሚል ክርክር አንስቷል፡፡
የቁጥጥር ቦርዱ እንደጻፈው ከሆነ "ፌስቡክ ባለፈው ጥር 7 ያስተላለፈውን እገዳ እንደገና በመመልከት በስድስት ወራት ውስጥ ትክክለኛው ውሳኔ ማሳለፍ አለበት"ም ነው ያለው፡፡
ፌስቡክን ጨምሮ ትዊተርና ዩትዩብ ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ምክር ቤት (ካፒታል ሂል) ላይ የተፈፀመውን ጥቃት አበረታተዋል በሚል እንዳገዷቸው ይታወሳል።
ይሁን እንጂ የቁጥጥር ቦርዱ ፌስቡክ ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውሳኔውን እንደገና ሊያጤን ይገባል ማለቱን ሲ.ኤን.ኤን ዘግበዋል፡፡
ይህንን ተከትሎም በትራምፕ ላይ የተላለፈው እገዳ ይነሳ ወይስ ይቀጥል በሚል ጉዳይ የፌስቡክ ኩባንያ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ኒክ ክሌግ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ኒክ በብሎጋቸው እንዳሰፈሩት ከሆነ “የተነሳው ትችት የምንቀበለው ቢሆንም በወቅቱ የወሰነው ውሳኔ ተገቢና አስፈላጊ እንደነበር እናምናለን፤ አሁን ቦርዱ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የወሰድነው እርምጃ እንደገና በማጤን ስድስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተገቢውን ውሳኔአችን የምናሳውቅ ይሆናል፤ እስከዛ ድረስ ግን እገዳው የሚጸና ይሆናል” ብለዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በፌስቡክና ኢንስታግራም ብቻ 60 ሚልዮን ተከታዮች እንደነበራቸው ይታወቃል፡፡