የአሜሪካ ሴኔት ዶናልድ ትራምፕ እንዳይከሰሱ ወሰነ
ሰባት የሪፓብሊካን ሴናተሮች እንዲከሰሱ ድምጽ ቢሰጡም ለክስ የሚያስፈልገውን 2/3 ድምጽ ማግኘት አልተቻለም
57 ሴናተሮች ትራምፕን ጥፋተኛ አድርገው እንዲከሰሱ ሲወስኑ 43ቱ ክሱን ተቃውመዋል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ለመልቀቅ ጥቂት ቀናት ሲቀሯቸው በካፒቶል ሂል ሁከትና ብጥብጥ ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በሥልጣን ዘመናቸው አወዛጋቢ እንደነበሩ ብዙዎች የሚገልጿቸው ዶናልድ ትራምፕ በካፒቶል ሂል የተከሰተውን ሁከት ጠርተዋል በሚል ተወቅሰዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በካፒቶል ሂል ተፈጥሮ በነበረው ሁከት ምክንያት የክስ ሂደት (ኢምፒችመንት) ሲካሄድባቸው የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎም በርካቶች በተለይም ዴሞክራቶች ትራምፕ እንዲከሰሱ ሲጠይቁ ነበር፡፡
ፕሬዝዳንቱ እንዲከሰሱ በኮንግረስ ከተወሰነ (ኢምፒችመንት ከተካሄደ) በኋላ ጉዳዩ ወደ ሴኔት ማምራቱ ይታወሳል፡፡ የሀገሪቱ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) አባላት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ይከሰሱ ወይስ አይከሰሱ በሚለው ጉዳይ ላይ ትናንት ድምጽ ሰጥተዋል፡፡
በዚህም መሰረት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔቱ) 100 አባላት ትናንትና በሰጡት ድምጽ 57 አባላት የቀድሞው ፕሬዝዳንት እንዲከሰሱ ሲወስኑ ቀሪዎቹ እንዳይከሰሱ ወስነዋል፡፡
2/3 ኛ የሚሆኑት የምክር ቤት አባላት ዶናልድ ትራምፕ እንዲከሰሱ ቢወስኑ ኖሮ ሕጉ ገቢራዊ ይሆን ነበር፡፡ ይሁንና 43 የሴኔት አባላት የቀድሞው ፕሬዝዳንት እንዳይከሰሱ ድምጽ በመስጠታቸው አሁን የትራምፕ ከመከሰስ ድነዋል፡፡
ትራምፕ እንዲከሰስ ከወሰኑት 50 የዴሞክራቲክ ፓርቲ ሴናተሮች ድምጽ በተጨማሪ ከሴኔቱ የሪፓብሊካን አባላት የ17 ሴናተሮች ድምጽ የሚፈለግ ቢሆንም የቀድሞው ፕሬዝዳንት እንዲከሰስ የወሰኑት 7 ሪፓብሊካኖች ናቸው፡፡ ሴኔቱ ዶናልድ ትራምፕ እንዲከሰሱ ቢወስን ፣ ሚስተር ትራምፕ ከዚህ በኋላ ለፕሬዝዳንትነት አይወዳደሩም ነበር፡፡
የሪፐብሊካኑ ሚች ማክ ኮኔል ምንም እንኳን ትራምፕ እንዳይከሰሱ ድምጽ ከሰጡት መካከል አንዱ ቢሆኑም ዶናልድ ትራምፕ በካፒቶል ሂል ተፈጥሮ ለነበረው ሁከት ተጠያቂ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሰረት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው አስቀያሚ ድርጊት እንዲፈጠር አድርገዋል ብለዋል፡፡ ይሁንና ክሱ ሕገ መንግስታዊ አይደለም ብለዋል ኮኔል፡፡ አሁንም ቢሆን ትራምፕ በፍርድ ቤት ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው ማክ ኮኔል የገለጹት፡፡
የዴሞክራት ተወካዮች ዶናልድ ትራምፕን እንዳይከሰሱ ማድረግ አደገኛ መሆኑን ሲገልጹ ፣ የትራምፕ ጠበቆች ደግሞ የክሱ ሂደት ከመጀመሪያው ጀምሮ በውሸት የተሞላ ነበር ብለዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከውሳኔው በኋላ ባወጡት መግለጫ ጠበቆቻቸውን እና ለሕገ መንግስት ቆመዋል ያሏቸውን ሴናተሮች አመስግነዋል፡፡