ሰዎች በህይወታቸው አብዝተው የሚጨነቁባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
“መጨነቅን አቁም ወይም ሁሉም ነገር ጥሩ ይሆናል” የሚሉ የአጽናኝ ምክሮች በጭንቀት ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች እምብዛም ትርጉም የላቸውም
የስነ ልቦና አማካሪዎች የበርካታ ሰዎች የጭንቀት መነሻ ጉዳዮች እና መፍትሄዎቻቸውን ጠቁመዋል
በህይወት ውጣ ውረድ ፣ ከፍራቻ ፣ ውሳኔን ለመወሰን ከመቸገር አልያም ይሆናል እና አይሆንም በሚሉ መካከሎች የሰው ልጅ ለጭንቀት ተጋላጭ ይሆናል፡፡
ከሰዎች ጋር ባለው መስተጋብር ፣ በሕይወት ማሳካት በሚፈልጋቸው ጉዳዮች መነሻ እንዲሁም በኑሮ የሚያጋጥሙ ውጣ ወረዶችን እንዴት ማለፍ እንደሚቻል አለማወቅ በርካቶች ጭንቀት እንዲፈጠርባቸው ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ቀዳሚዎቹ እንደሆኑ የስነ ልቦና ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡
ጭንቀት አስደናቂ የሆኑ ገጠመኞችን እንደሚያበላሽ፣ በዙሪያችን ያሉት ሲተኙ በጨለማ ውስጥ እረፍት አጥቶ እንደሚያስተክዝ ፣ ህይወትንም ጣዕሟን እንደሚያሳጣ የሚናገሩት ባለሙያዎቹ፤ “ጭንቀት በጣም መጥፎውን እንድትፈራ ሊያደርግህ ይችላል፤ ነገር ግን ህይወትህን እንዲያበላሸው አትፍቀድ” ሲሉ ይመክራሉ፡፡
ዘ ጋርዲያን ከተለያዩ የስነልቦና ባለሙያዎች ጋር ቆይታ አድርጎ ባሰባሰበው መረጃ ሰዎችን አብዘተው የሚያስጨነቁ ጉዳዮች ናቸው ያላቸውን ነጥቦችን ዘርዝሯል፡፡
1. በነገሮች ውድቀት ሊያጋጥመኝ ይችላል ወይም ውጤታማ ላልሆን እችላለሁ በሚል መጨነቅ
የሰው ልጅ የልምድ ፣ የትምህርት ፣ የቤተሰብ እና የውሳኔዎቹ ውጤት ነው የሚሉት የስነልቦና ባለሙያዎቹ ሰዎች አዲስ ነገር መሞከርን እና ውድቀትን እንዳይፈሩ ያበረታታሉ፡፡
ህይወት መውደቅ መነሳት ፣ ከስህተት መማር እንደሆነ ሲነገር የሰው ልጅ ሁሌም ቀጥተኛ በሆነ መንገድ የሚሄድ ከሆነ አልያም ፈተናዎችን እያለፈ ወደ ስኬቱ የማይጓዝ ከሆነ የህይወት ጣዕሟን አያውቅም ተብሏል፡፡
በአንድ ነገር ላይ መውደቅ ማለት ሙሉ ለሙሉ ውድቀት ማለት አይደለም ይልቁንም አንድ ነገር እንዳሰብከው አልሰራም ማለት ነው፡፡
ስህተት የሚሰራ ሰው የሚሞክር በመሆኑ በትላንት ወይም ስለስህተት ብቻ እያሰቡ ከመጨነቅ ከጥፋት ተምሮ ነገን ስለማቅናት ማሰብ ይገባል ነው የተባለው፡፡
2. እሞታለሁ ብሎ መፍራት (ስለሞት መጨነቅ)
መቀየር በማይችሉት የህይወት አጋጣሚ የሚጨነቁ ሰዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደልም ከዚህ መካከል ሞት አንዱ ነው፡፡
ስለሞት አብዝተው ከመጨነቃቸው የተነሳ ምሽታቸውን በቅዠት የሚያሳልፉ ፣ እንቅልፍ አጥተው በድብርት የሚሰቃዩ ሰዎችን በተደጋጋሚ እንደሚያጋጥማቸው የስነልቦና ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡
የሰው ልጅ በምድር የሚኖረው አንድ ግዜ ነው ሰለማይቀር ነገር መጨነቅ በእጃችን ላይ በሚገኙ መልካም ነገሮች ላይ እንዳናተኩር ከማድረጉም በላይ ተስፋን አሳጥቶ በአንድ ቦታ እንድንቆም ያደርጋል፡፡
ሞት የህይወት ተቃራኒ እንደመሆኑ ሰዎች በምድር ቆይታቸው በተለመዱ የህይወት ኡደቶች ከመጠመድ ባለፈ ዛሬን መኖር አካባቢያችን ከሚገኙ ቤተሰብ እና ወዳጆች ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ይበረታታል፡፡
ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም እንዲሉ ሞትን ፍራቻ ዛሬን መኖር ማቆም ተገቢ አይደለም ፡፡
3. በሰዎች አይን በቂ አይደለሁም ብሎ ማሰብ
“ሌሎች አንተን የሚመለከቱብህን መነጸር ከማሰብ በፊት አንተ እራስህ የምታይበትን እይታ አስተካክል”፡፡
ሰዎች የሚገምቱህ ፣ የሚጠሉህም ሆነ የሚወድሁ ራስህን በገለጽክበት ወይም ነኝ ብለህ ባሰብክበት ልክ ነው ይላሉ የስነ ልቦና ባለሙያዎች፡፡
በቅድሚያ ሰዎች በሁሉም ነገር ውጤታማ እና ምልዑ (ፐርፌክት) እንዳልሆኑ ማሰብ በሰዎች አይን ሞልቶ ስለመታየት እንዳይጨነቁ የሚያደርጋቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡
አቅምን እና ድክመትን ለይቶ ማወቅ እሱን መቀበል እንዲሁም ያልሆኑትን ሆነው ለመታየት የማይሞክሩ ሰዎች በሌሎች የሚኖራቸው ተቀባይነት አያስጨንቃቸውም፡፡
እውነተኛ ፣ ግልጽ እና እራሳቸውን የሚሆኑ ሰዎች ድክመት ቢኖርባቸው እንኳን ሌሎች ስለእነርሱ የሚያስቡት ነገር የሚያሳስባቸው አይሆንም ስለዚህ ከሁሉም በላይ እራስን እንደራስ መቀበል ትልቅ የህይወት ስኬት ነው፡፡
ሰዎች አይረዱኝም ፣ መጥፎ ነገር ሊያጋጥመኝ ይችላል ፣ እምወዳቸውን ሰዎች ላጣ እችላለሁ እና ሰዎችን ልጎዳ እችላለሁ የሚሉ ሀሳቦች ለበርካቶች ጭንቀት መነሻ ከሚሆኑ ጉዳች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡