ዓለማችን በጭንቀትና በድብርት ምክንያት በየዓመቱ 1 ትሪሊዮን ዶላር እያጣች እንደሆነ ተገለጸ
በዓለማችን አንድ ቢሊዮን ህዝብ የአዕምሮ ጤና ህመምተኞች እንዳሉ ተገልጿል
በአዕምሮ ጤና ምክንያት 12 ቢሊዮን የስራ ሰዓት እየባከነ እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል
ዓለማችን በጭንቀት ምክንያት አንድ ትሪሊዮን ዶላር እያጣች እንደሆነ ተገለጸ።
የዓለም ጤና ድርጅት እና የዓለም ሰራተኞች ድርጅት በጋራ በመሆን በአዕምሮ ጤና ዙሪያ ያጠኑትን ጥናት ይፋ አድርገዋል።
እንደ ጥናቱ ከሆነ ከዓለማችን ጠቅላላ ህዝብ ውስጥ አንድ ቢሊዮን ያህሉ የአዕምሮ ህመምተኞች ናቸው።
እንዲሁም 15 በመቶ የሚሆነው የአለማችን ሰራተኛ ማህበረሰብ ከአዕምሮ ህመም ጋር አብሮ እንደሚኖር ተገልጿል።
በዓለማችን በአዕምሮ ጤና እክል ምክንያት 12 ቢሊዮን የስራ ሰዓት በጭንቀት እና ድብ ርት ምክንያት እንደሚባክን በጥናቱ ላይ ተገልጿል።
ሲጂቲዌን አፍሪካ የሁለቱን ተቋማት የጥናት ውጤት ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ በአዕምሮ ጤና እክል ምክንያት በሚባክነው ሰዓት አንድ ትሪሊዮን ዶላር ባክኗል።
በመሆኑም የአለማችን አሰሪ ተቋማት ለሰራተኞቻቸው ደህንነት ሊጠነቀቁ ይገባል የተባለ ሲሆን ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠር እና ለሰራተኞች አሉታዊ አመለካከቶች ትኩረት እንሲሰጡም ጥሪ ቀርቧል።
በተለይም ሰራተኞችን ለድብርት እና ጭንቀት የሚዳርጉ ተደራራቢ የስራ ጫናዎች፣ አሉታዊ አመለካከቶችን አለማረም እና ሌሎች ምቾት የሚነሱ ድርጊቶችን ተከታትሎ ማስተካከል እንደሚገባም በጥናቱ ላይ ተጠቁሟል።
ከዓለማችን ሀገራት መካከል 35 በመቶዎቹ ብቻ ስለ አዕምሮ ጤና ፕሮግራሞችን ቀርጸው በመስራት ላይ ናቸው የተባለ ሲሆን ኮሮና ቫይረስ ችግሩን የበለጠ እንሳሰፋውም ተገልጿል።
መንግስታት ለአዕምሮ ጤና ስራዎች ከጠቅላላ በጀታቸው ቢያንስ ሁለት በመቶ እንዲመድቡም በምክረ ሀሳብነት ቀርቧል ተብሏል።
ለሰራተኞች የአዕምሮ ህመም መንስኤዎች በስራ ቦታ ሰራተኞችን ማመናጨቅ፣ ማግለል እና አድሎዓዊ አሰራሮች ተጨማሪ ምክንያቶች እንደሆኑም በጥናቱ ላይ ተገልጿል።
በመሆኑም ተቋማት ለሰራተኞቻቸው አዕምሮ ጤንነት እንዲጠነቀቁ ፣ ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠርና ፍትሀዊ አሰራሮችን እንዲከተሉ የዓለም ጤና ድርጅት አሳስቧል።