በኬንያ ይገኛል የተባለው የ550 ልጆች አባት ግን እስካሁን ምንም ምላሽ አልሰጠም
ሆላንዳዊው ከ550 በላይ የሚሆኑ ልጆች አባት “በልጁ እናት” ክስ ተመሰረተበት።
ይህ ዜና እንዴት አንድ ሰው 550 ልጆችን ይወልዳል? የሚል የግርምት ጥያቄን ማስነሳቱ አይቀርም።
የ41 አመቱ ጆናታን ትዳር መስርቶ አልያም ከተለያዩ ሚስቶች አይደለም 550 ልጆች የወለደው፤ በመላው አለም የዘር ፍሬውን (ስፐርሙን) በመላክ እንጂ።
በሆላንድ አንድ ሰው የዘር ፍሬውን ከ25 ጊዜ በላይ መስጠት አይችልም። ከዚህ ካለፈ በሚወለዱት ልጆች የአዕምሮና አካላዊ ጤና ላይ ከፍ ያለ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርም ይገልጻል።
ጆናታን ግን “ዶነርካይንድ ፋውንዴሽን” ለተሰኘ ተቋም ህጉን በመጣስና የዘር ፍሬውን ደጋግሞ በመስጠት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ህጻናት አባት ሆኗል ነው የተባለው።
የጆናታንን የዘር ፍሬ ወስዳ ልጅ ካገኙ እናቶች አንዷም “በልጇ አባት” ላይ ክስ መመስረቷን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።
“ከመቶ በላይ ልጆች አባት መሆኑን ባውቅ ኖሮ ከሱ የዘር ፍሬ (ስፐርም) ወስጄ አልወልድም ነበር” ስትልም ተናግራለች ክሱን የመሰረተችው እናት።
ጆናታን በፈረንጆቹ 2017 በመቶዎች ለሚቆጠሩ ልጆች መፈጠር ምክንያት መሆኑ የሆላንድ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት እንደሳበ የሀገሪቱ የዘር ፍሬ ባንኮች እና ክሊኒኮች የግለሰቡን የዘር ፍሬ እንዳይቀበሉ መመሪያ ተላልፎላቸው እንደነበር ተዘግቧል።
ይሁን እንጂ የ41 አመቱን ግለሰብ ከ550 በላይ ልጆች “አባት” ከመሆን አላስቆሙትም ብለዋል የሀግሪቱ መገናኛ ብዙሃን።
ጎልማሳው በአሁኑ ወቅትም በማህበራዊ ሚዲያዎች የዘር ፍሬውን ለበርካታ ሴቶች ለመስጠት ቅስቀሳ እንደሚያደርግ ነው የተነገረው።
አሁን በኬንያ ይገኛል የተባለ ጆናታን በቁጥጥር ስር ውሎ ህጻናትን ለአዕምሮና አካላዊ ጤና ችግር ከመዳረግ መታደግ ይገባል የሚሉት የ”ዶነርካይንድ ፋውንዴሽን” ጠበቃ ማርክ ደ ሄክ፥ የወንድ የዘር ፍሬ የሚቀበሉ ክሊኒኮች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።