በደቡብ አፍሪካ አንድ ሴት ባንድ ጊዜ 10 ልጆችን ወለደች
እንስቷ ላለፉት ሰባት የእርግዝና ወራት በርካታ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን እንዳሳለፈች ተናግራለች
10 ወላዷ ጎሲያም የችርቻሮ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ስትሆን ባለቤቷ ግን ስራ ፈላጊ ነው
በደቡብ አፍሪካ የጎቴንግ ከተማ ነዋሪዋ ጎሲያም ታማራ ሲቶል የ37 ዓመት እድሜ ያላት ሰትሆን ባንድ ጊዜ ሰባት ወንዶችን እና ሶስት ሴት ልጆችን በፕሪቶሪያ ሆስፒታል በሰላም መውለዷ ተሰምቷል።
ባንድ ጊዜ የ10 ልጆች እናት የሆነችው ይህች ደቡብ አፍሪካዊት በፕሪቶሪያ ሆስፒታል በሰላም መገላገሏን የጀርመን ድምጽ (DW) አፍሪካ ዘግቧል።
እንስቷ ከአንድ ወር በፊት በአንድ ጊዜ ዘጠኝ ልጆችን በመውለድ በሞሮኳይቷ እንስት ተይዞ የነበረውን የዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ የግሏ ማድረጓም ተገልጿል።
ከዚህ በፊት የ6 ዓመት እድሜ ያላቸው መንታ ልጆች እናት የሆነችው ይህች እናት በተፈጥሯዊ መንገድ አርግዛ ያሳለፈቻቸው 9 የእርግዝና ወራት ፍጹም ሰላማዊ እንደነበሩ ተናግራለች።
ይህች እንስት ባለቤት ሶቴሲ ለጋዜጠኞች እንዳለው 10ሩን ልጆች በሰባት ወሯ እንደወለደቻቸው ገልጾ አሁን ጥያቄ አታብዙብኝ ደስ ብሎኛል ነገ እናወራለን ሲል መናገሩ ተዘግቧል።
የልጆቹ እናት ባንድ የችርቻሮ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ስትሆን ባለቤቷ ግን ስራ ፈላጊ ነው።
ባንድ ጊዜ የ10 ልጆች እናት የሆነችው ይህች እንስት ለእርግዝና ክትትል ወደ ህክምና ተቋም አምርታ ከሀኪሞቿ የሰማችው መረጃ እንዳስደነገጣት ተናግራለች።
“በመጀመሪያ ሀኪሞቹ ስድስት ልጆችን እንዳረገዝኩ ነገሩኝ፤ በዚህ ደንግጬ ሳለ በተደረገልኝ ተጨማሪ ምርመራ ደግሞ ከማህጸን ውጪ ሁለት መንታዎች ማለትም አራት ልጆችን እንዳረገዝሁ ተነገረኝ” ብላለች የባሰ መደንገጧን በመጠቆም።
ከዚያም በተደረገልኝ ተጨማሪ ህክምና የእርግዝና ጊዜዬ ህመም እና አስጨናቂ ጊዜ ባሳልፍም ጥሩ ነበር በመጨረሻም 10ሩንም ልጆቼ በሰላም በመውለዴ ደስተኛ ነኝ ስትል ተናግራለች።