ልዩልዩ
በወረርሽኝ እና ተላላፊ በሽታዎች ጉዳይ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች አማካሪ በኮሮና ተያዙ
በዚህም ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋ መገናኘት ማቆማቸው ነው የተነገረው
በቁንጮ የተላላፊ በሽታዎች ምሁርነታቸው የሚታወቁት ዶ/ር ፋውቺ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል ተብሏል
በተላላፊ በሽታዎች ቁንጮ ምሁርነታቸው የሚጠቀሱት አሜሪካዊ በኮሮና ተያዙ።
ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን የአሜሪካ ብሔራዊ የጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
ማጠናከሪያዎቹን ጨምሮ ሁለት ያህል ጊዜያት የቫይረሱን ክትባቶች የወሰዱት የ81 ዓመቱ አዛውንት በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ ተገልለው እንደሚቆዩና ከቤታቸው እንደሚሰሩ ተገልጿል።
ፋውቺ ለመጀመሪያ ጊዜ በቫይረሱ መያዛቸውን የሚመሩት ብሔራዊ የአለርጂ እና ተላላፊ በሽታዎች ተቋም አስታውቋል።
ይህን ተከትሎ አዛውንቱ ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም ሆነ ከሌሎች የሙያ ባልደረቦቻቸው ጋር እየተገናኙ እንዳልሆነ ነው ተቋሙ ያስታወቀው።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማካሪ የነበሩት ዶ/ር አንቶኒዮ ፋውቺ አሁንም ፕሬዝዳንት ባይደንን እያማከሩ መሆኑ ይታወቃል።
እንደ ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃዎች ከሆነ በዩናይትድ ስቴትስ በምርመራ የተረጋገጡ 85 ሚሊዮን የኮሮና ቫይረስ ኬዞች አሉ።
እስካሁንም ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሞተዋል።