አንድ የቻይና ባለስልጣን ዋሽንግተን የታይዋንን ነጻ ሃገርነት እንደማትደግፍ ብትገልጽም እየተገበረችው አይደለም ብለዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሀገራቸው የታይዋንን ነጻ መሆን እንደማትደግፍ በተደጋጋሚ ቢገልጹም ይህ ተግባራዊ አለመሆኑን የቻይና ባለስልጣን አስታወቁ፡፡ በቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የውጭ ጉዳይ ኮሚሽን ዳይሬክተር ያንግ ጅኢች ከአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው ይህንን ያሉት፡፡
የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ከቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ የውጭ ጉዳይ ኮሚሽን ዳይሬክተር ያንግ ጅኢች ጋር በሉግዘንበርግ ተወያተዋል፡፡ ውይይታቸው ውጤታማ እንደነበር ቢገለጽም፤ አሜሪካ ቻይናን “እየበደለች ነው” ሲሉ የቻይናው ባለስልጣን ጠቅሰዋል፡፡
የሁለቱ ወገኖች ውይይት ቀደም ብሎ በስልክ የታቀደ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን በቀጣይ የሀገራቱ መሪዎች እንዲወያዩ ዕድል ሊሰጥ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ አሜሪካ እና ቻይና በሰብዓዊ መብት ጥሰት፤ በታይዋን ጉዳይ፤ በንግድ እና በወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የቆየ አለመግባባት አላቸው፡፡
የቻይናው ባለስልጣን፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ ሌላ የቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ መግባት እንደማይፈልጉና የታይዋንን ነጻ ሀገር መሆን እንደማይደግፉ በተደጋጋሚ ቃል ቢገቡም ይህንን ግን አሜሪካ እየጣሰች ነው ብለዋል፡፡
አሜሪካ አሁን ላይ የዋሸንግተንንና የቤጅንግን ግንኙነት ወደ መጥፎ ሁኔታ እየመራችው እንደሆነም የቻይናው ተወካይ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ቻይና ከአጋሮቿ ጋር ትብብር እንዳታደርግ አሜሪካ እንቅፋት እንደማትሆን በተደጋጋሚ ብትገልጽግም ቃሏን አልጠበቀችም ተብሏል፡፡
የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን በቤጅንግ እና በዋሸንግተን መካከል ቀጥተኛ ንግግር ማድረግ ውድድሩን ለመምራት ያግዛል ማለታቸውን ኋይት ሃውስ አስታውቋል፡፡