የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ቤት በኤፍ ቢ አይ ተፈተሸ
የአሜሪካ ፖሊስ የቀድሞውን የሃገሪቱን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መኖሪያ ቤትን በርብረዋል፡፡
በፍሎሪዳ የሚገኘውን የትራምፕን መኖሪያ የፈተሸው የፌዴራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍ.ቢ.አይ) መሆኑን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
ፍተሻው ዶናልድ ትራምፕ ምናልባትም በደጋፊዎቻቸው ከተፈጸመው የካፒቶል ሂል ጥቃት ጋር በተያያዘ ከቤተ መንግስት ያሸሹት ሚስጥራዊ ሰነድ ይኖር ይሆን በሚል የተካሄደ ነው መሆኑን ሲ.ኤን.ኤን ዘግቧል፡፡
ትራምፕ ኒውዮርክ በሚገኘው ህንጻቸው ላይ ሳሉ ነው መኖሪያቸው የተፈተሸው።
"ማር-ኤ-ላጎ የሚገኘው ቅንጡ መኖሪያ ተከቦ ነው የሚገኘው፤ በብዙ የኤፍ.ቢ.አይ ፖሊሶች ተወርሮም ይገኛል" ሲሉ ዶናልድ ትራምፕ ሶሻል ትሩዝ በተሰኘ ማህበራዊ ሚዲያቸው አስታውቀዋል።
በቀጣዩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ (2024) እንዳይወዳደሩ ለማድረግ በማሰብ የተደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ዶናልድ ትራምፕ በፈረንጆቹ 2024 ለሚካሄደው ምርጫ ለመወዳደር ያላቸውን ፍላጎት በይፋ ባይገልጹም፣ ባለፉት ጥዊት ወራት ለመወዳደር ፍላጎት እንዳላቸው ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ትራምፕ ከካፒቶል ሂሉ ጥቃት እንዲሁም የተሸነፉበትን የምርጫ 2020ን ውጤት በኃይል ለመቀየር ሞክረዋል፤ ሌሎች ሚስጥራዊ ሰነዶችንም አሽሽተዋል ከመባሉ ጋር በተያያዘ በምርመራ ላይ መሆናቸው ይታወቃል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት በየትኛውም የቀድሞ የአሜሪካ መሪ ላይ ያልተደረገ በሚል ድንገተኛውን ፍተሻ ተቃውመዋል።
"ይህ በየትኛውም የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ላይ ተደርጎ የማያውቅ ነው" ሲሉም ነው ትራምፕ ድንገተኛውን ፍተሻ አስመልክተው ባወጡት መግለጫ ድርጊቱን ያወገዙት።
የፍትህ ስርዓቱን መበላሸት ከማሳየቱም በላይ ለግራ ዘመም ዴሞክራቶች መጠቀሚያ መሆኑን የሚያሳይም ነው ብለዋል።
እንዲህ ዐይነቱ ድርጊት በሶስተኛው ዓለም ባሉ ሃገራት ብቻ የሚደረግ እንደሆነም ነው በመግለጫው ያስቀመጡት።
ከአሁን ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በሙስና ተዘፍቃለች ያሏት አሜሪካ ከእነዚህ ሃገራት መካከል አንዷ እየሆነች ስለመምጣቷም አስፍረዋል።
ሆኖም የሶስተኛው ዓለም ሃገራት እነማን እንደሆኑ አላስቀመጡም።