ዶናልድ ትራምፕ በየቀኑ የ10 ሺህ ዶላር ቅጣት እንዲከፍሉ ተፈረደባቸው
የአሜሪካ ፍርድ ቤት ዶናልድ ትራምፕ የታክስ ሰነዶችን አላቀረቡም በሚል ቅጣት ያስተላለፈባቸው
የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የታክስ ሰነዶችን እስከሚያቀርቡም በየቀኑ በገንዘብ ይቀጣሉ ተብሏል
የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታክስ ሰነዶችን ለማቅረብ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው በየቀኑ የሚከፍሉት የገንዝብ ቅጣት ተፈረደባቸው።
የዩናይትድ ስቴትስ ፍርድ ቤት በትናትናው እለት በዋለው ችሎት ነው “ዶናልድ ትራምፕ የሂሳብ እና የታክስ ሰነዶችንበተጠየቁበት ወቅት አላቀረቡም” በሚል የገንዘብ ቅጣት ያስተላለፈባቸው።
በዚህም የአሜሪካ ፍርድ ቤት ዳኛ አርተር ኢንጎሮን፤ ዶናልድ ትራምፕ በፍርድ ቤት የታዘዙትን የሂሳብ እና የታክስ ሰነዶችን እስከሚያቀርቡ ድረስ በየቀኑ በ10,000 የአሜሪካ ዶላር ቅጣት እንዲከፍሉ አዘዋል።
የኒውዮርክ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሌቲሺያ ጀምስ፤ ዶናልድ ትራምፕ ሰነዶቹን እንዲያቀርቡ የተቀመጠው ቀነ ገደብ በመጋቢት ወር ማለፉን አስታውቀው፤ ትራምፕ በተባለው ጊዜ ዘነዶቹን አለማቅረባቸው የፍርድ ቤት ውሳኔን እንደናቁ ተደርጎ እንዲያዝ ጠይቀዋል።
ለዓመታት በትራምፕ ድርጅት ውስጥ የታክስ ማጭበርበርን ሲመረምሩ የቆዩት አቃቤ ህግ ሌቲሺያ ጀምስ፤ “ዶናልድ ትራምፕ የፍርድ ቤቱን ትእዛዝ አክብረው የሂሳብ እና የታክስ ሰነዶችን እስከሚያቀርቡ ድረስ በየቀኑ 10 ሺህ ዶላር የቅጣት ገንዘብ ይከፍላሉ” ብለዋል።
የዶናልድ ትራምፕ ጠበቃ በበኩላቸው በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ይግባኝ እንደሚሉ ተናግረዋል።
የኒውዮርክ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የትራምፕ ድርጅት ዝቅተኛ ቀረጥ ለመክፈል እንዲሁም ከባንክ ለመበድር የማጭበርበር ተግባር ፈጽሟል በማለት ጠርጥሯቸዋል።
የአሜሪካ የቀድሞ ፐሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ቤተሰባቸው ድርጊቱን አልፈጸምንም ሲሉ ክደው ተከራክረዋል።