ዶናልድ ትራምፕ “በስልጣን ላይ ብሆን ኖሮ የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት አይከሰትም ነበር” ብለዋል
የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ ዓለም ጦርነት እያስገባን ነው ሲሉ መተቸታቸው ተሰምቷል።
ዶናልድ ትራምፕ ባሳለፍነው ሰኞ ከኒውስ ማክስ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ “ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለዩክሬን ጦርነት ሲሉ የአሜሪካን ብሄራዊ ኢኮኖሚ እያራቆቱ ነው” ብለዋል።
“ይህ ደግሞ ሄዶ ሄዶ በዩክሬን ጉዳይ ወደ ዓለም ጦርነት ያስገባናል” ሲሉም ትራምፕ ተናግረዋል።
የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አክለውም “እስካሁን በስልጣን ላይ ብሆን ኖሮ ሩሲያ ወደ ዩክሬን አትሄድም፤ የዩክሬን ጦርነትም አይከሰትም ነበር” ብለዋል።
በፈረንጆቹ 2024 በሚካሄደው የአሜሪካ ምርጫ ላይ የመወዳደር ሀሳብ እንዳላቸው ያስታወቁት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ “በምርጫው ከመወዳደር የሚያስቆመኝ ነገር አለ ብዬ አላስብም” ሲሉም ተናግረዋል።
የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባሳለፈነው ሚያዝያ ወር ላይም፤ “ጆ-ባይደን አሜሪካን እያዋረዳት ስለሆነ በ2024 ድጋሚ ለምርጫ ልወዳደር እችላለሁ” በማለት ፍንጭ መስጠታቸው ይታወሳል።
ትራምፕ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር፤ "ከመጀመሪያው በበለጠ በሁለተኛ ጊዜ በጣም የተሻለ ነገር እሰራለሁ፤ እናም ይህንን ማድረግ አለብን፤ እኔን ለሁለተኛ ጊዜ ስወዳደር ማየት ሚፈልግ ሰው አለ ?” የሚል ጥያቄም አቅርበዋል።
በ2024፣ ከሁሉም በላይ፣ ቆንጆ፣ ቆንጆ እና ቆንጆ የሆነውን ዋይት ሀውስን እንመልሰዋለን" ሲሉም ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል።
እንደፈርነጆቹ በ2020 በአሜሪካ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ጆ-ባይደን ድል ቢቀዳጁም አወዛጋቢው ትራምፕ ምርጫው ተጭበርብሯል በማለታቸው ደጋፊዎቻቸው በርካታ ድርጊቶች ሲፈጽሙ እንደነበር ይታወሳል።
ደጋፊዎቻቸው በተለይም በዋሽንግተን የሚገኘውን የካፒቶል ህንፃ የወረሩበት ክስተት፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በዴሞክራሲ ረዥም ርቀት ተጉዛለች በምትባለው ሀገረ አሜሪካ ይሆናል ብሎ ያልጠበቀው ትልቅ ግርምት የፈጠረ አጋጠሚ ነበር።