ትራምፕ የባለፈው ዓመቱን የካፒቶል ሂል ግርግር አቀናብረዋል በሚል ተጠርጥረዋል
የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርገዋል በሚል ተከሰሱ።
ዶናልድ ትራምፕ የተከሰሱት ከአንድ ዓመት በፊት ደጋፊዎቻቸው በአሜሪካ ምክር ቤት ወይም ካፒቶል ሂል ከፈጠሩት ግርግር ጋር በተያያዘ መሆኑ ተነግሯል።
በካፒተል ሂል ግርግር ተከትሎ በዴሞክራቶች የሚመራው የአሜሪካ ምክር ቤት ኮሚቴ በማዋቀር ክስ የመስማት ሂደት ትናት ጀምሯል።
በችሎቱ ላይ የተገኙት የሪፐብሊካን አባል እና የኮሚቴ ምክትል ሊቀ መንበር ሊዝ ቼኒ፤ የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምክር ቤቱ ህንጻ ላይ የተቀነባበረው ጥቃት እንዲፋፋም አድርገዋል ብለዋል።
የዴሞክራት ፓሪቲዋ ባይን ቶምሰን በበኩላቸው፤ ዶናልድ ትራምፕ ባቀነባበሩት ብጥብጥ የአሜሪካ ዴሞክራሲ አደጋ ላይ ወድቆ እንደበረ አስታውቀዋል።
የኮሚቴው ሰብሳቢ እና ሚሲሲፒ የህግ አውጪው ቶምፕሰን ለችሎቱ እንደተናገሩት፤ “ጥር 6 የተካሄደው ግርግር የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ነበር፤ አላማውም መንግስትን ለመገልበጥ ነው” ብለዋል።
"ሁከቱ በድንገት አልነበረም” ያሉት፤ ቶምፕሰን ይህ የትራምፕ የመጨረሻ አቋም ነበር” ሲሉም ተናግረዋል።
የካፒቶል ሂል ግርግር ዙሪያ ለአንድ ዓመት ምርመራ ሲካሄድ ከቆየ በኋላ ነው በዴሞክራቶች የሚመራው የአሜሪካ ምክር ቤት ኮሚቴ በማዋቀር ክሱን ትናነት ምሽት መስማት የጀመረው።
ክስ የመስማት ሂደቱ ላይም የግርግሩን ሁኔታ የሚያሳይ ቪዲዮ እና ሌሎችም ማስረጃዎች መቅረባቸው ተነግሯል።
በቀረበው ቪዲዮ ላይም የአሜሪካ የቀድሞ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢል ባር፤ “ዶናልድ ትራምፕ ምርጫው ተጭበርብሯል ሲሉ የሚያቀርቡት ክስ መሰረተ ቢስ ነው” ማለታቸው ተደምጧል።
በቪዲዮው ላይ የዶናለድ ትምፕ ልጅ ኢቫንካ ትራምፕ ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ምርጫውን በተመለከተ የሰጡት አስተያየት ትክክል አይደለም የሚለውን ሃሳብ መደገፏን የሚያሳይም ተካቷል።
በ2024 በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት ሊወዳደሩ እንደሚችሉ ፍንጭ የሰጡት ዶናልድ ትራምፕ የክስ መስማት ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት በሰጡት አስተያየት፤ የቀረበባቸው ክስ “የፖለቲካ አጀንዳ ያለው የፈጠራ ወሬ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
ባለፈው ዓመት ጥር 6 ነበር ነውጠኛ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች በአሜሪካ ይሆናል ተብሎ በማይጠበቅ ሁኔታ ካፒቶል ሒልን ሰብረው በመግባት ብጥብጥ የፈጠሩት።
ነውጠኛ የትራምፕ ደጋፊዎች ካፒቶል ሒልን ሰብረው ሲገቡ በወቅቱ የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት የጆ ባይደንን መመረጥ ለማጽደቅ በውይይት ላይ እንደነበሩ ይታወሳል።