የውልደት ምጣኔ በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰባቸው ሀገራት
በ97 የአለም ሀገራት የችግሩ መጠን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል
ባደጉት ሀገራት ያሉ ሴቶች ለትምህርት እና ስራ ቅድሚያ መስጠታቸው ምጣኔው እንዲቀንስ ዋነኛ ምክንያት ነው ተብሏል
የውልደት ምጣኔ መቀነስ በአለም አቀፍ ደረጃ የስነ-ህዝብ ፖሊሲን በማዛባት ከፍተኛ ስጋትን ደቅኗል፡፡
ደቡብ ኮርያ ፣ ቻይና እና ጃፓንን የመሳሰሉ ሀገራት በእርጅና እድሜ ላይ የሚገኙ ዜጎቻቸው ቁጥር ሲጨምር በአንጻሩ የአምራች ሀይላቸው እና የውልደት ምጣኔያቸው በማሽቆልቆል ላይ ይገኛል፡፡
የውልደት ምጣኔ ማለት አንድ ሴት በህይወት ዘመኗ የምትወልዳቸው ልጆች በአማካኝ የሚሰላበት ስሌት ነው፡፡
በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የሚገኙ ሴቶች ከሚገኙበት ዝቅተኛ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አንጻር በፍጥነት ወደ ትዳር መግባታቸው እና በቂ የወሊድ መቆጣጠርያ መድሀኒቶች አቅርቦት ባለመኖሩ የውልደት ምጣኔያቸው ከፍተና ሲሆን ፤ በአንጻሩ ባደጉት ሀገራት የሚገኙ ሴቶች ለስራ እና ትምህርት ቅድሚያ መስጠታቸው በሀገራቱ የውልደት ምጣኔ እንዲቀንስ ምክንያት ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡
በፈረንጆቹ 2016 በአለም አቀፍ ደረጃ 142 ሚሊየን ህጻናት ሲወለዱ ይህ ቁጥር በ2021 ወደ 129 ሚሊየን አሽቆልቁሏል፡፡
በ2023 ከፍተኛ የውልደት ምጣኔ አላቸው ከተባሉ 46 ሀገራት መካከል 44ቱ ከሰሀራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ናቸው፡፡
በ2100 ከሰሀራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚወለዱ ህጻናት ከግማሽ በላዩን ድርሻ እንደሚይዙ የአለም ባንክ ትንበያ ያመላክታል፡፡
ከ1950-2021 የውልደት ምጣኔያቸው በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰባቸው ከሚገኙ ሀገራት መካከል ደቡብ ኮርያ ቀዳሚዋ ስትሆን የሀገሪቱ የውልደት መጠን በ86 በመቶ መቀነሱ ነው የተገለጸው። ቻይና ፣ ታላንድ እና ጃፓን በቅደም ተከተል በደረጃው ተቀምጠዋል፡፡