የቻይና ህዝብ ቁጥር ከእድገት ወደ ማሽቆልቆል
ከ1950 ጀምሮ በህዝብ ብዛት ትመራ የነበረችው ቻይና ከ2022 ጀምሮ የዜጎቿ ቁጥር እየቀነሰ ነው
የመንግስታቱ ድርጅት ትንበያ እንደሚያሳየው የቻይና የህዝብ ቁጥር በ2100 በ1970 ወደነበረበት ይመለሳል
ቻይና የመንግስታቱ ድርጅት የሀገራትን የህዝብ ቁጥር መመዝገብ ከጀመረበት 1950 ጀምሮ በህዝብ ብዛት ከአለማችን ቀዳሚዋ ሀገር ነበረች።
በ1950 የሀገሪቱ ህዝብ ቁጥር ከ552 ሚሊየን በላይ እንደነበርም ይነገራል።
ቻይና በ2022 የህዝብ ቁጥሯ 1 ነጥብ 42 ቢሊየን ደርሷል፤ ይህም ከአፍሪካ አህጉር ጠቅላላ ህዝብ የሚስተካከል፤ የአውሮፓ እና አሜሪካ ህዝብ ድምርን የሚበልጥ ነበር።
ይሁን እንጂ እስያዊቷ ሀገር ከ2022 ጀምሮ የህዝብ ቁጥሯ መቀነስ ጀምሮ በ2023 የአለማችን ባለብዙ ህዝብ ሀገር መሪነቷን በህንድ መነጠቋ ይታወሳል።
ቤጅንግ በ1980 ያስተዋወቀችው የ”አንድ ህጻን” ፖሊሲ የህዝብ ብዛት እድገቷን እንደገታው ይታመናል።
አንዲት ቻይናዊ አንድ ብቻ ልጅ እንድትወልድ የሚያደርገው ፖሊሲ በ2016 ወደ ሁለት ልጅ፤ በ2021 ደግሞ ወደ ሶስት ልጅ ከፍ እንዲል ቢደረግም በአጭር ጊዜ ለውጥ ያመጣል ተብሎ አይጠበቅም።
የህዝብ ቁጥር ባለበት እንዲቀጥል አንዲት ሴት ሁለት ልጆችን መውለድ ይጠበቅባታል፤ በቻይና ግን አማካይ የውልደት ምጣኔው ከ2 በታች (1 ነጥብ 7) ነው።
የውልደት ምጣኔው በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የቻይና ህዝብ ቁጥር በ2050 ወደ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን፤ በ2100 ደግሞ ወደ 800 ሚሊየን ዝቅ ሊል እንደሚችል የመንግስታቱ ድርጅት ትንበያ ያሳያል።