የውጭ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ "የውክልና ጦርነት" ከፍተዋል-ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በዚህ ንግግራቸው የውጭ ጠላቶች የሚላቸውን በስም አልጠቀሷቸውም
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያ በቀጠናው ጎልታ ትወጣለች በሚል ስጋት የውስጥ ግጭቶችን እያባባሱ ናቸው ብለዋል
የውጭ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ "የውክልና ጦርነት" ከፍተውባታል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ተናገሩ።
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ይህን ያሉት የ128ኛውን የአድዋ ድል በዓል አስመልክቶ 'በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም' በነበረው ዝግጅት ላይ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር ነው።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ኢትዮጵያ ባላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጧ እና በታሪኳ ምክንያት "ምንጊዜም በክፉ የሚመለከቷት የውጭ ጠላቶች አሏት" ብለዋል።
"እነዚህ የውጭ ጠላቶች የኢትዮጵያን ሰራዊት ፊት ለፊት ተዋግተው ማሸነፍ እንደማይችሉ ያውቃሉ። በቀደሙት ጊዜያት በተለያዩ የሀገሪቱ ጠረፎች ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ባካሄዷቸው ጦርነቶች አሳፋሪ ሽንፈት ተከናንበዋል።"
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በዚህ ንግግራቸው የውጭ ጠላቶች የሚላቸውን በስም አልጠቀሷቸውም።
የውጭ ጠላቶች፣ ኢትዮጵያውያን ያለፉትን ጦርነቶችን ያሸነፉት በአንድነት በመቆም መሆኑን ተገንዝበዋል ያሉት ፊልድ ማርሻሉ በቀጥታ ከመግጠም ይልቅ የውስጥ ክፍፍል ፈጥሮ ማዳከምን መርጠዋል ብለዋል።
ፊልድ ማርሻሉ የውጭ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ ጦር ከማዝመት ይልቅ "እርስ በእሰርስ የሚያጋጭ ትርክት በመፍጠር ከፋፍሎ በማዳከም እና ባንዳዎችን ቀጥረው የውክልና ጦርነት እንዲያካሂዱላቸው ማድረግን መርጠዋል" ሲሉ ተደምጠዋል።
እነዚህ የውጭ ጠላቶች የሀገር ፍቅር ስሜት የሌላቸውን ዜጎች "ሀገራቸውን እንዲወጉ በመመልመል በገንዘብ እና በትጥቅ" በመደገፍ የውክልና ጦርነቱን አጠናከረው መቀጠላቸውን ፊልድ ማርሻሉ አክለው ገልጸዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ እንዳሉት ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ እነዚህ ጠላቶች ኢትዮጵያ በቀጠናው ጎልታ ትወጣለች በሚል ስጋት የውስጥ ግጭቶችን እያባባሱ ናቸው።
"ከለፉት አምስት አመታት ወዲህ 'ነጻ አውጭ ነን፣ የህዝብ ጥያቄ ተሸክመናል' እያሉ ወደ ውጊያ የገቡ ኃይሎች በተጨባጭ እያስፈጸሙ ያሉት የውጭ ጠላቶቻችን ተልእኮ" ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ይህን የማይገነዘብ ኢትዮጵያዊ "የሀገራችንን ሁኔታ ያልገነዘበ መሆን አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።
- በአማራ ክልል በመከላከያ የተገደሉባቸውን ቤተሰቦቻቸውን መቅበር የተከለከሉ አሉ - አምነስቲ
- በአማራ ክልል የድሮን ጥቃት” እንደሚቀጥል የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ተናገሩ
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ "በትጥቅ እና በሚዲያ የሚደገፉ ታጣቂ ኃይሎች" በተለያዩ ቦታዎች አሳት በመለኮስ የመከላከያ ሰራዊት በስምሪት እንዲወጠር እና እንዲዳከም ሰርተዋል ብለዋል።
ታጣቂ ቡድኖቹ መከላከያው የውጭ ጠላት ቢመጣ መከላከል እንዳይችል ለማድረግ ሰርተዋል ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ 'እንታገልለታለን' የሚሉትን ህዝብም ለችግር ዳርገዋል ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ የታጣቂ ቡድኖቹ ዋና ኃይላቸው መደምሰሱን የገለጹት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ "በቅርብ ጊዜ ግብአተ መሬታቸው ይፈጸማል" ሲሉ ተናግረዋል።
"አዲስ አበባን በጥቂት ቀናት እንቆጣጠራን ያሉ ህልመኞችም" እንቅስቃሴም በመከላከያ እና በጸጥታ ኃይሎች መምከኑን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ተናግረዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ለውጭ ኃይሎች የተገዙ "ባንዳ" ሲሉ የጠሯቸው ታጣቂ ቡድኖች የትኞቹ እንደሆኑ በስም አልጠቀሱም።
ነገርግን በአሁኑ ወቅት መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል መንግስት በሽብር ከፈረጀው 'ከኦነግ ሸኔ' እና ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር የትጥቅ ግጭት እያካሄደ ይገኛል።
በተለይም በአማራ ክልል ባለፈው አመት ሚያዝያ ወር ከክልል ልዩ ኃይሎች መፍረስ ጋር በተያያዘ የተነሳው የትጥቅ ግጭት የፌደራል መንግስትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ አስገድዶታል።
መንግስት ባለፈው ሀምሌ ወር የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥር መጨረሻ ጊዜው ሲጠናቀቅ "የሚቀሩ ስራዎች" እንዳሉ በመጥቀስ ለተጨማሪ አራት ወራት አራዝሞታል።
በግጭቱ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በንጹሃን ላይ በርካታ ግድያ መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና ሌሎች የመብት ተቋማት ተደጋጋሚ ሪፖርት አውጥተዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከወራት በፊት በመንግስት መገናኛ ብዘኻን በተላለፈ ቃለ መጠይቅ ሰላማዊ ሰዎችን በማይጎዱበት ሁኔታ በድሮን ጭምር ጥቃቱ እንደሚቀጥል መናገራቸው ይታወሳል።