ሁሉም የፊፋ አባል ፌደሬሽኖች 1.5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የሚያገኙ ሲሆን ብድርም መጠየቅ እንደሚችሉ ተገልጿል
ፊፋ በፈተና ላይ ለሚገኘው እግር ኳስ የሚውል 1.5 ቢሊዮን ዶላር የእርዳታ ፈንድ አፀደቀ
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳደር አካል ፊፋ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ሊጎችን ለመታደግ በድጋፍ እና በብድር መልክ የሚቀርብ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ማጽደቁን አስታውቋል፡፡
የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ “የእርዳታ ፈንዱ በምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ድምፅ የፀደቀ ሲሆን ገንዘቡ እንዴት እንደሚወጣ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል” ብለዋል ፡፡
ሁሉም የፊፋ 211 አባላት እያንዳንዳቸው 1 ሚሊዮን ዶላር “በመሰረታዊ የአንድነት ድጋፍ” እንዲሁም 500,000 ዶላር ለሴቶች እግር ኳስ መዋል ያለበት ይቸራሉ ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ሁሉም አባል ማህበራት (ፌደሬሽኖች) የዓመታዊ ገቢያቸውን 35 በመቶ ያህል ከኮቪድ 19 ማገገሚያ ብድር መጠየቅ እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን ፣ የሚጠይቁት ከፍተኛ የብድር መጠን አምስት ሚሊዮን ዶላር መብለጥ እንማይችል ተገልጿል፡፡ አህጉራዊ የእግር ኳስ አስተዳደር አካላት 2 ሚሊዮን ዶላር በድጋፍ መልክ የሚያገኙ ሲሆን ተጨማሪ 4 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት ማመልከት ይችላሉ፡፡
“በገንዘቡ አጠቃቀም ረገድ በኦዲት የታገዙ ጥብቅ ቁጥጥሮች” እንደሚደረጉ ቃል የገቡት ኢንፋንቲኖ ብድሮች እንዴት እንደሚመለሱም “በጣም ግልፅ ሁኔታዎች” ይቀመጣሉ ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የተቋረጠው የእግር ኳስ ውድድር በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች እንዳልተጀመረ የጠቀሱት የፊፋ ፕሬዝዳንት ኢንፋንቲኖ “ክለቦች እና ፌደሬሽኖች በችግር ዉስጥ በመሆናቸው ልንረዳቸው ይገባል” ብለዋል፡፡
ፊፋ ካዘጋጀው ፈንድ ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው ከተቀማጭ ገንዘቡ የሚሸፈን እንደሆነ የ ኤኤፍፒ ዘገባ ያመለክታል፡፡