የአረብ እግር ኳስ ለዓለም ብዙ እያበረከተ መሆኑን የፊፋው ፕሬዚዳንት ኢንፋንቲኖ ገለጹ
በቪዲዮ የታገዘ የእግር ኳስ ዳኝነትን ለኳስ ፍትሐዊነት አስተዋጽኦ እንዳለው የፊፋ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል
ወደፊት በእግር ኳስ ዘርፍ የአረቡ ዓለም አስደናቂ ነገሮችን እንደሚያሳይ ኢንፋንቲኖ ተናግረዋል
የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) ፕሬዚዳንት ጂያን ኢንፋንቲኖ የአረብ እግር ኳስ ለዓለም ስፖርት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስታወቁ፡፡
ኢንፋንቲኖ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዱባይ ከተማ ተገኝተው ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ የአረብ እግር ኳስ እንደ መሃመድ ሳላህና ሪያድ ማህሬዝን የመሳሰሉ ኮኮቦችን በማፍራቱ ለዓለም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡ የሊቨርፑሉ መሐመድ ሳላህ እና የማንቸስተር ሲቲው ሪያድ ማህሬዝን ያፈራው የአረብ እግር ኳስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ዕድገት ማሳየቱን በመጥቀስም አድንቀዋል፡፡
የአረቡ ዓለም ከ 450 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የያዘ አካባቢ ሲሆን ለዓለም እግር ኳስ ብዙ እያበረከተ መሆኑን ገልጸው የአረብን ስነ ልቦና የሚረዳ ሰው አረቦች ለእግር ኳስ ምን ያህል ስሜት እንዳላቸው ይረዳል ብለዋል፡፡ ለዚህም ማሳያው “እግር ኳስ ላይ ብዙ ኢንቨስትመንት ማፍሰሳቸው ነው” ያሉት ኢንፋንቲኖ ወደፊት በእግር ኳስ ዘርፍ በአረቡ ዓለም አስደናቂ ነገሮችን ልናይ እችላለን ሲሉም ለአል ዐይን ኒውስ ተናግረዋል፡፡
“የአረብ ባህልን የሚመለከት ማንኛውም ሰው በውስጡ ምን ያህል ስሜት እንደሚኖር ያውቃል ፤ እየተፈናቀሉ ያሉ ኢንቨስትመንቶችን ሲመለከቱ ደግሞ መጪው ጊዜ በአረቡ ዓለም የበለጠ አስገራሚ ነገሮችን ይሰጠናል ብዬ አስባለሁ” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ኢንፋንቲኖ በመጪው ዓመት በሚካሄደው የአረብ ዋንጫ ፣ “ምርጥ የአረብ እግር ኳስ ክለቦችን ማየት እንድንችል ፊፋ ድጋፍ ያደርጋል” ብለዋል፡፡
“መጪው ጊዜ የአረብን እግር ኳስ አቅም ያሳየናል” ያሉት ፕሬዚዳንቱ በቪዲዮ የታገዘ የእግር ኳስ ዳኝነትን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፣ ቴክኖሎጂው እግር ኳስን እንደሚያግዝ ፣ለእግር ኳስ የበለጠ ፍትህ እንደሚሰጥ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ ቴክኖሎጂው እንደ እግር ረዥም እድሜ ያለው ሳይሆን የሁለት ዓመት ዕድሜ እንዳለው መረዳት እንደሚገባ፣ ወደፊት እየዳበረና እየተሻሻለ እንደሚሄድ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡