የመጨረሻው የጋዛ ረቂቅ የተኩስ አቁም ስምምነት ለእስራኤልና ሀማስ ቀረበ
አደራዳሪዎች ሰነዱን ያቀረቡት የፕሬዝደንት ባይደንና ትራምፕ መልእክተኞች የተገኙበት ንግግር ውጤታማ ሆኖ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው
አሜሪካ፣ ኳታር እና ግብጽ በጋዛ ያለውን ጦርነት ለማስቆም ከአንድ አመት በላይ ሲሰሩ ቆይተዋል
የመጨረሻው የጋዛ ረቂቅ የተኩስ አቁም ስምምነት ለእስራኤልና ሀማስ ቀረበ።
የፕሬዝደንት ባይደን እና ትራምፕ መልእክተኞች የተገኙበት ንግግር ውጤታማ ሆኖ ከተጠናቀቀ በኋላ አደራዳሪዎች ለእስራኤል እና ለሀማስ የመጨረሻውን ረቂቅ የስምምነት ሰነድ በዛሬው እለት መስጠታቸውን ሮይተርስ በጉዳዩ ላይ መረጃ ያላቸውን ባለስልጣን ዘግቧል።
ባለስልጣኑ እንደገለጹት የተኩስ አቁም ማድረግን እና የታጋቾች መልቀቅን በተመለከተ የተዘጋጀውን ሰነድ ኳታር የእስራኤል ሞሳድና የሽን ቤት ስለላ ኃላፊዎች እና የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር በተገኙበት ንግግር ላይ ለሁለቱም አቅርባለች።
ትራምፕ በቀጣይ ሳምንት ወደ ኃይትሀውስ ሲገቡ የአሜሪካ መልእክተኛ የሚሆኑት ስቲቭ ዊትኮፍ በንግግሩ ተካፍለዋል። የተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ባይደን አስተዳደር መልእክተኛ ብሬት ማክግሩክም በቦታው ተገኝተዋል።
"ቀጣዩ 24 ሰአታት ስምምነት ላይ ለመድረስ ውሳኝ ነው" ያሉት ባለስልጣኑ ረቂቅ ስምምነቱ ሰኞ ጠዋት የተካሄዱ ፍሬያማው ውይይቶች ውጤት ነው ብለዋል።
የእስራኤል ካን ሬዲዮ የእስራኤል ባለስልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው በኳታር ያሉት የእስራኤል እና የሀማስ ልኡክ ቡድኖች ረቂቅ ስምምነቱን መቀበላቸውን በዛሬው እለት ዘግቧል።
እስራኤል፣ ሀማስ እና የኳታር የውጭ ጉዳይ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡት ጠይቆ ምላሽ አለማግኘቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
በሁለቱም በከል ያሉት ባለስልጣናት የመጨረሻው ረቂቅ መዘጋጀቱን ከመግለጽ ቢቆጠቡም መሻሻሎች እንዳሉ አመላክተዋል። ከፍተኛ የእስራኤል ባለስልጣን እንዳሉት ሀማስ ለረቂቅ የስምምነት ሀሳቡ በጎ ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ በጥቂት ቀናት ውስጥ ስምምነት ላይ ይደረሳል ብለዋል። ለንግግሩ ቅርብ የሆኑ የፍልስጤም ባለስልጣን ደግሞ ንግግሩ "በጣም ተስፋ ሰጭ ነው"፤ "ልዩነቶች ጠባዋል። ሁለም በጎ ከሆነ ከስምምነት ለመድረስ ትልቅ ግፊት አለ" ብለዋል።
አሜሪካ፣ ኳታር እና ግብጽ በጋዛ ያለውን ጦርነት ለማስቆም ከአንድ አመት በላይ ሲሰሩ ቆይተዋል። ነገርግን ሀገራቱ እስካሁን ያደረጉት ጥረት ስኬታማ አልነበረም።
ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን ለማቆም እና ታጋቾችን እስራኤል ውስጥ ባሉ ፍልስጤማውያን እስረኞች ለመለዋወጥ በመርህ ደረጃ የተስማሙት ከወራት በፊት ነበር። ነገርግን ሀማስ ሊኖር የሚችል ማንኛውንም ስምምነት ወደ ዘላቂ ተኩስ አቁም ማምራት አለበት የሚል አቆም የያዘ ሲሆን እስራኤል ደግሞ ሀማስ ሙሉ በሙሉ ሳይደመሰስ ጦርነት እንደማታቆም በተደጋጋሚ ገልጻለች።