የአውሮፓ ሀገራት በሶሪያ ላይ ተጥለው የነበሩ ማዕቀቦችን ለማንሳት ሊመክሩ ነው
ህብረቱ ማዕቀቦቹን ለማንሳት አካታች መንግስት ማቋቋምን በቅድመ ሁኔታ አቅርቧል
በትላንትናው ዕለት የመካከለኛው ምስራቅ እና የምዕራባውያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የተሳተፉበት ጉባኤ በሳኡዲ አረብያ ተካሂዷል
የአውሮፓ ሀገራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በበሽር አላሳድ መንግስት ወቅት ተጥለው የነበሩ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ማዕቀቦችን ለማንሳት ሊመክሩ መሆኑ ተነግሯል፡፡
በተያዘው ወር መጨረሻ (ከ14ቀናት በኋላ) ቀጠሮ የያዙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሀገሪቱ እያደረገች የምትገኘውን ሽግግር ለመደገፍ ምን አይነት ማዕቀቦችን ማንሳት እንደሚኖርባቸው ይመክራሉ ነው የተባለው፡፡
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ካጃ ካላስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ጥር 27 በሚኖራቸው ጉባኤ የአውሮፓ ሀብርት አባላት በሶሪያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ እንዴት ማቃለል እንደሚኖርባቸው ሀሳብ ያቀርባል ብለዋል፡፡
ከ13 አመታት የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ከአንድ ወር በፊት በሃያት ታህሪር አል ሻም (ኤችቲኤስ) በሚመራ አማፂ ሃይሎች ፈጣን ጥቃት ከስልጣን የተወገዱ ሲሆን ቡድኑ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በደማስቆ ውስጥ ጊዜያዊ መንግስት ለማዋቀር በጥረት ላይ ይገኛል።
ማንኛውም የሶሪያን ማዕቀብ ለማቃለል የሚደረግ የአውሮፓ ህብረት ውሳኔ በአዲሱ የሶሪያ መንግስት የአስተዳደር አካሄድ ላይ ቅድመ ሁኔታን ያስቀመጠ ነው፡፡
ይህም የተለያዩ ቡድኖችን እና ሴቶችን ማካተት ፣አክራሪነትን ማስወገድ ፣ የሰብአዊ እና ሌሎች የዜጎችን መብት ማክበርን ያጠቃልላል፡፡
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ካጃ ካላስ "ሁኔታዎች ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እየተጓዙ እንደሆነ ካየን ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ለመስራት ዝግጁ ነን ፤ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ የማይሄድ መሆኑን ካየን ደግሞ ወደ ኋላ ልንመለስ እንችላለን" ብለዋል፡፡
የአሳድ መወገድን ተከትሎ በሶሪያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ እና አለም አቀፍ እርዳታዎች ያለገደብ እንዲደረጉ ስትጠይቅ የነበረችው ሳኡዲ አረብያ፤ በትላንትናው ዕለት ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት እና ከምዕራባውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በሶሪያ ጉዳይ ስብሰባ አካሂዳለች፡፡
በጉባኤው ላይ የብሪታንያ ፣ሳውዲ አረቢያ፣ ግብፅ፣ የአረብ ኢምሬትስ፣ ኳታር፣ ባህሬን፣ ኢራቅ፣ ዮርዳኖስ፣ ሊባኖስ ፣ ቱርክ እንዲሁም የተመድ የሶሪያ ልዩ መልዕክተኛ ተሳትፈዋል፡፡
የሳኡዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሃን አል ሳዑድ ከጉባኤው በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “በሶሪያ ላይ የተጣለውን የአንድ ወገን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማዕቀብ በፍጥነት የማይነሳ ከሆነ በሀገሪቱ ልማትን የማሳካት ፍላጎት ላይ እንቅፋት ይሆናል” ብለዋል።
አሜሪካ ለ6 ወር የሚቆይ የኢነርጂ ግብይት እንዲኖር በመንግስት በኩል የሚደረጉ የሰብአዊ እና ሌሎችም ድጋፎች ከአሜሪካ እገዛ እንዲደረግላቸው እና ሌሎችንም የማዕቀብ ማቀለያዎች ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች፡፡
ጀርመን በበኩሏ በአሳድ መንግስት ወቅት ተጠያቂ የነበሩ ባላስልጣናት ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን ለማስቀጠል ጎን ለጎን ጊዜዊ መንግስቱን ለመደገፍ ፈቃደኛ መሆኗን አስታውቃለች፡፡
እንደ ህብረት የብራሰልሱ ተቋም የሚያነሳቸው ማዕቀቦች ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ የሚያደርጉትን ስብሰባ ተከትሎ ከ14 ቀናት በኋላ የሚታወቅ ይሆናል፡፡