ወጣቷ የፊንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር አደገኛ እጽ አለመውሰዳቸው በምርመራ ተረጋገጠ
ተቃዋሚዎች ጠቅላይ ሚኒስትሯ ለወጣቶች አርዓያ አይደሉም በሚል ስልጣን እንዲለቁ ግፊት ሲያደርጉ ነበር
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከሰሞኑ ሲጨፍሩ መታየታቸውን ተከትሎ ትችቶች ሲቀርብባቸው ነበር
ወጣቷ የፊንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳና ማሪን አደገኛ እጽ አለመውሰዳቸው በምርመራ ተረጋገጠ፡፡
ከሰሞኑ የ35 ዓመቷ የፊንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳና ማሪን “አልኮል ጠጥታ ከጓደኞቿ ጋር ስትደንስ የሚያሳይ ቪዲዮ” ሾልኮ ከወጣ በኋላ አነጋገሪ መሆኑ ይታወሳል፡፡
በዚህም የሳና ማሪን የአደናነስ ሁኔታ ጥያቄ የፈጠረባቸው የሀገሪቱ ተቃዋሚዎች፤ አደንዛዥ ዕጽ ወስዳ ከነበረ ምርመራ እንድታደርግ መጠየቃቸው አይዘነጋም፡፡
ተቃዋሚዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ያደረገቸው ድርጊት አርዓያ እንዳልሆነ ስልጣን እንድትለቅ ቢጠይቁም የ36 አመቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪና ግን “አደንዛዥ ዕጽ አልወሰድኩም” ስትል ተደምጣለች፡፡
በሞቀ ጭፈራ ላይ እንደነበረች የገለጸችው ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪና የ”አልኮል መጠጥ” መውሰዷን ግን አልሸሸገችም፡፡
ማሪና ከጓደኞቿ ጋር በሞቅታ ስትደንስ የሚያሳው ቪዲዮ ሾልኮ በመውጣቱ መበሳጨቷ ብትገለጽም፤ የሚቀርቡ ትችቶች ሚዛናዊ አይደሉም ብላለች፡፡
ይሁንና ትችቶቹ እየጨመረ መምጣታቸውን ተከትሎ የአደገኛ እጽ መውሰዷን እና አለመውሰዷን የሚያስረዳ ምርመራ ለማድረግ ተገዳለች፡፡
የዚህ ምርመራ ይፋ የሆነ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ሳሪና አደገኛ እጽ አለመውሰዳቸው በምርመራ መረጋገጡን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከምርመራ ውጤት ይፋ መሆን በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትሯ “በህይወቴ አደገኛ እጽ የሚባል ወስጄም አፌ ውስጥም ገብቶ አያውቅም“ ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሳሪና የኮኬይን፣ ካናቢስ፣ ኦፒዮድስ እና ሌሎች በአደገኛ እጽ የተመደቡ ምርቶችን መውሰድ አለመውሰዳቸውን የሚያሳዩ ምርመራዎች ተደርጎላቸዋል ተብሏል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በርካታ የጠቅላይ ሚኒስትር ሳሪና ደጋፊዎች ድጋፋቸውን ለማሳየት የተለያዩ መጠጦችን በብርጭቆ በመያዝ ፎቶ እየተነሱ በማህበራዊ ትስስር ገጾች በማጋራት ላይ ናቸው፡፡