በደቡብ አፍሪካ ቴብል ተራራ የተቀሰቀሰው እሳት ታሪካዊ ቅርሶች ላይ ጉዳት ማድረሱ ተነገረ
የእሳት አደጋው በሳለፍነው እሁድ ረፋድ ላይ ነው የተቀሰቀሰው
በአካባቢው የሚኖሩ በርካታ ሰዎች እና የኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከስፍራው እንዲወጡ ተደርጓል
በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ከተማ በሚገኘው ቴብል ተራራ የተቀሰቀሰው እሳት ታሪካዊ ቅርሶችን እና ህንፃዎችን ማውደሙ ተነግሯል።
በተጨማሪም በኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ ግቢ የሚገኙ ታሪካዊ ቤተ መፅሐፍት እና ህንፃዎችም ጉዳት እንደደረሰባቸውም ሮይተርስ ዘግቧል።
ኬፕታውን ከተማ ከንቲባ ዳን ፕላቶ በበኩላቸው፤ እሳት አደጋው በቴብል ተራራ ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ የሚገኝ እና በ400 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ እጽዋትን ማውደሙን ተናገረዋል።
በአካባቢው የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ከአካባቢው ለቀው ለመውጣት የተገደዱ ሲሆን፤ ኬፕታውን ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በተራራው አቅራቢያ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ከስፍራው ለማውጣት ተገደዋል።
እሳት አደጋው በሳለፍነው እሁድ የተቀሰቀሰ ሲሆን፤ አደጋውም ሆን ተብሎ ተቀስቅሷል ነው የአካባቢው ባለስልጣናት የሚሉት።
ከእሳት አደጋው ጋር ተያይዞም እስካሁን አንድ ተጠርጣሪ ባሳለፍነው እሁድ ምሽት በቁጥጥር ስር ስለመዋሙ ተነግሯል።
በአሁኑ ወቅትም የደቡብ አፍሪካ የእሳት አደጋ ተቆጣጣሪዎች እሳቱን ለማጥፋት ርብርብ እያደረጉ መሆኑንም ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።
በዚህም ውሃ መርጫ ሄሊኮፕተሮች እና 250 የእሳት ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች እሳቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት እያደረጉ ናቸው።
ባለሙያዎቹ በአሁኑ ጊዜ እሳቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል ተቃርበዋል የተባለ ሲሆን፤ የቃጠሎ አደጋ የደረሰባቸው ሁለት ባለሙያዎች ህክምና ላይ እንደሚገኙ ነው የተነገረው።