ከፕሬዝዳንቱ ጋር የነበረ ግለሰብ በኮሮና መያዙ በመረጋገጡ ነው ፕሬዝዳንቱ ራሳቸውን የለዩት
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ለይቶ ማቆያ ገቡ
የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር እና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎዛ ለይቶ ማቆያ መግባታቸውን የፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
የፕሬዚዳንቱ ተጠባባቂ ቃል አቀባይ ታይሮኔ ሳአል እንዳሉት ቅዳሜ ዕለት ፕሬዚዳንቱ በተገኙበት በተደረገ የእራት ግብዣ ላይ የተገኘ አንድ ግለሰብ በኮሮና ቫይረስ መያዙን ተከትሎ ነው እራሳቸውን የለዩት፡፡ ምንም አንኳን ፕሬዚዳንቱ ራሳቸውን ለይተው ቢያቆዩም እስካሁን የኮሮና ቫይረስ ምልክት እንዳላሳዩ ቃላ አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡
እንደ ኒውስ 24 ዘገባ ሲሪል ራማፎዛ በእራት ግብዣው ላይ የነበረውና የኮሮና ቫይረስ የተገኘበት ግለሰብ ቶሎ አገግሞ ሙሉ ጤነኛ እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡
እራት ግብዣው የተደረገው ለአንድ የትምህርት ቤት ፋውንዴሽን ገንዘብ ለማሰባሰብ እደነበርና ፋውንዴሽኑም የሲሪል ራማፎዛ ፋውንዴሽን አጋር እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ግብዣው የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጡ ሕጎችን በጠበቀ መንገድ በሀገሪቱ የንግድ ከተማ ጆሃንስበርግ በሚገኝ ሆቴል የተደረገ ሲሆን 35 ሰዎችም ተሳታፊዎች ነበሩ ተብሏል፡፡
የሕዳሴ ግድቡን ድርድር የሚመሩት ሲሪል ራማፎዛ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት ተጀምሮ ለ7 ሳምንታት የተቋረጠው የሕዳሴ ግድብ ድርድር ትናንት ጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲጀመር ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡