በደቡብ አፍሪካ የኮሮና ወረርሽኝ በፍጥነት እየቀነሰ መሆኑን ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ገለጹ
በሀገሪቱ በየዕለቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአማካይ በ 7,000 ቀንሷል
በሀገሪቱ በወረርሽኙ ምክንያት የተጣሉ እገዳዎች እንደሚላሉ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል
በደቡብ አፍሪካ የኮሮና ወረርሽኝ በፍጥነት እየቀነሰ መሆኑን ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ገለጹ
ባለፉት ሶስት ሳምንታት በደቡብ አፍሪካ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየቀነሰ በሆኑን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ገለጹ፡፡
ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት በየዕለቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከ 12’000 ወደ 5,000 ዝቅ ብሏል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ወረርሽኙን በማስመልከት ትናንት ባደረጉት ንግግር ምንም እንኳን በአጠቃላይ በሀገሪቱ ኮሮና የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 583,653 ቢሆንም አሁን ላይ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር ግን 105,000 ገደማ ነው ብለዋል፡፡ ይህም የተጠቂዎች ቁጥር በፍጥነት እየቀነሰ መሆኑን እንደሚያመለክት ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል፡፡
በቫይረሱ ተይዘው በየዕለቱ ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች ቁጥርም በወሩ መጀመሪያ ከነበረው 10,000 ገደማ ወደ 4,000 መዉረዱንም ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ገልጸዋል፡፡ ይህም የሆስፒታሎችን ጫና በከፍተኛ መጠን እየቀነሰ ነው፡፡
በትንሹ 11,667 ሰዎች በኮሮና ሳቢያ ህይወታቸውን እንዳጡ የተናገሩት ራማፎሳ 80 በመቶ የሚሆኑ ታማሚዎች ከቫይረሱ ማገገማቸውንም ገልጸዋል፡፡
ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ 5 ወራት ተቆጥረዋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ሀገራቸው በዚህ ልክ የከፋ ችግር አጋጥሟት እንደማያውቅ አብራርተዋል፡፡ ይህም በሀገሪቱ እና በህዝቦቿ ኢኮኖሚ ፣ የጤና ስርዓት እና በህዝቡ የዕለት ተእዕለት ህይወት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳሳረፈ ነው ራማፎሳ ያነሱት፡፡
በአሁኑ ወቅት የወረርሽኙ ተጽዕኖ እየቀነሰ መሆኑን በመጥቀስ ለዚህም ህዝባቸው ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በወረርሽኙ ምክንያት የተጣሉ እገዳዎችን መንግስት ማላላት እንደሚጀምርም ፕሬዝዳንቱ ተናግረወል፡፡ ይሁንና እገዳዎች መላላታቸውን ተከትሎ ቫይረሱ ይበልጥ እንዳያገረሽ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ አብዛኛው ሰው ወደ ስራ በሚመለስበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ የማያደርግ ከሆነ የሚመጣው ጊዜ ካለፈው ይበልጥ አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል በንግግራቸው ወቅት አንስተዋል፡፡ በመጀመሪያ ዙር የሚነሱ እገዳዎች ዉጤት ተገምግሞ በሁለተኛ ዙር እገዳዎች ሙሉ በሙሉ እንደሚነሱም ቃል ገብተዋል፡፡
ደቡብ አፍሪካ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥር በዓለማችን አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
ዘገባው የቱዴይ ኒውስ አፍሪካ ነው፡፡