ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ከስልጣን ለማንሳት ያለመው ምርመራ በሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራል ተባለ
ፕሬዝዳንት ባይደን ከልጃቸው ጋር በተያያዘ ህግ ጥሰዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል
የፕሬዝዳንቱ ልጅ ሀንተር ባይደን በግብር ስወራ እና ሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥረው ክስ ተመስርቶባቸዋል
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ከስልጣን ለማንሳት ያለመው ምርመራ በሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራል ተባለ፡፡
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከልጃቸው ሀንተር ባይደን ጋር በተያያዘ ስልጣን ያላግባብ ተጠቅመዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን የአሜሪካ ህግ መወሰኛ ምክር ቤትም በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ኬቪን ማካርቲ እንዳሉት በፕሬዝዳንት ባይደን ላይ የቀረበባቸውን ከስልጣን ይነሱ ጥያቄ መቀበላቸውን እና ምክር ቤቱም የሙስና፣ ስልጣን አጠቃቀም እና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ምርመራውን ይቀጥላል ማለታቸውን ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
በዚህም መሰረት በፈረንጆቹ መስከረም 28 ማለትም ከአንድ ሳምንት በኋላ ምርመራው ይጀመራል የተባለ ሲሆን የሕገ መንግስት እና ሌሎች ህጎች ዙሪያ ትኩረቱን እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
የፕሬዝዳንት ባይደን የበኩር ልጅ የሆነው ሀንተር ባይደን የአሜሪካንን ህግ በመተላለፍ የተለያዩ የቢዝነስ ስምምነቶችን አድርገዋል ይህም የሆነው በአባቱ እውቅና እና ድጋፍ ነው የሚል ክስ በተደጋጋሚ እየቀረበ ይገኛል፡፡
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ማካርቲ ባሳለፍነው ሳምንት እንዳሉት ፕሬዝዳንት ባይደን ከልጃቸው ጋር በተያያዘ ግልጽ የህግ ጥሰት ስለመፈጸሙ ማስረጃዎች ተገኝተዋል ብለው ነበር፡፡
የፕሬዝዳንት ባይደን ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ኢያን ሳምስ በበኩላቸው በፕሬዝዳንት ባይደን ላይ የቀረበውን ክስ በወቅቱ መተቸታቸውም አይዘነጋም፡፡
የሪፐብሊካን ምክር ቤት አባላት ላለፉት ዘጠኝ ወራት በፕሬዝዳንት ባይደን ላይ ምርመራ ሲያደርጉ መቆየታቸውን እና መረጃ አለማግኘታቸውንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
ሀንተር ባይደን በፌደራል ምርመራ ስር ሆነው ጉዳያቸው እየተመረመሩ ናቸው የተባለ ሲሆን በውጭ ሀገራት ከሚያንቀሳቅሷቸው ቢዝነሶች ጋር በተያያዘ ግብር ሰውረዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ባይደንም በተለይም በፕሬዝዳንት ኦባማ የስልጣን ዘመን ጀምሮ ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ ለልጃቸው ያልተገባ የሕግ ከለላ አድርገዋል በሚል ትችቶችን እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡
በአሜሪካ ህገ መንግስት መሰረት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የሙስና ምርመራ ግኝት ከተገኘባቸው እና ሌሎች ከባድ ወንጀሎችን ፈጽመው ከተገኙ በቀጥታ ከስልጣን እንዲነሱ ያስገድዳል፡፡
ይሁንና በፕሬዝዳንቱ ላይ የደረጋል የተባለው ምርመራ በሀገሪቱ ምክር ቤት አባላት አብላጫ ድምጽ መጽደቅ ይጠበቅበታል፡፡