የአሜሪካ ምክር ቤት ከሰሞኑ ፕሬዝዳንት ባይደን ከስልጣን እንዲነሱ የሚጠይቅ ምርመራ እንደሚጀምር መግለጹ አይዘነጋም
የፕሬዝዳንት ባይደን የበኩር ልጅ ክስ ተመሰረተባቸው።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልጅ የሆኑት ሀንተር ባይደን ከሙስና እና ግብር ስወራ ጋር በተያያዘ ህግ ጥሰዋል በሚል ምርመራ ሲካሄድባቸው ቆይቷል።
የዚህ ምርመራ አንድ አካል የሆነው ውጤት ይፋ የሆነ ሲሆን በአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በስልጣን ላይ ባሉት ፕሬዝዳንቱ ልጅ ላይ ክስ መመስረቱ ተገልጿል።
የዴላዌር ፍርድ ቤት በሀንተር ባይደን ላይ ሶስት የወንጀል ክሶችን መመስረቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
በሀንተር ባይደን ላይ የተመሰረቱባቸው ክሶች በህግ የጦር መሳሪያ እንዳይዝ ተከልክሎ እያለ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት እና ህገ ወጥ መድሀኒትን በመጠቀም ላይ ያተኮሩ እንደሆኑ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በልጃቸው ላይ የተመሰረተው ክስ በሚቀጥለው ዓመት ለሚያደርጉት ዳግም ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል ተብሏል።
በተለይም ሀንተር ባይደን ከአሜሪካ ውጪ በሚያንቀሳቅሷቸው የንግድ ስራዎች ዙሪያ ግብር ሰውረዋል የሚል ተጨማሪ ምርመራ እየተካደባቸው ይገኛል ተብሏል።
የአሜሪካ አፈ ጉባኤ ኬቪን ማካርቲ ከሰሞኑ ፕሬዝዳንት ባይደን የህግ ጥሰት ስለመፈጸማቸው መረጃዎች ተገኝተዋል ማለታቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ባይደን ለልጃቸው ልዩ ከለላ እና ሽፋን ሰጥተዋል በሚል በሙስና ወንጀል ምርመራ እንደሚደረግባቸው ተገልጿል።
በልጃቸው ሀንተር ባይደን ላይ የጥፋተኝነት ውሴኔ ከተላለፈ በሀገሪቱ ህገ መንግሥት መሰረት ከስልጣን እንዲነሱ ሊደረጉ ይችላሉም ተብሏል።