ፕሬዝዳንት ባይደን በኢትዮጵያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ለተጨማሪ ዓመት አራዘሙ
በኢትዮጵያ ያለው አሁናዊ ሁኔታ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስጋት መሆኑ ተገልጿል
ከሁለት ዓመት በፊት የተጣለው ይህ ማዕቀብ ከቀናት በኋላ ያበቃ ነበር ተብሏል
ፕሬዝዳንት ባይደን በኢትዮጵያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ለተጨማሪ ዓመት አራዘሙ፡፡
አሜሪካ ከሁለት ዓመት በፊት የተቀሰቃሰው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የአሜሪካንን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ይጎዳል በሚል ነበር ጦርነቱ እንዲቆም ጫና ስታደርግ የቆየችው፡፡
ይህ ጦርነት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ምስራቅ አፍሪካን ይጎዳል የምትለው አሜሪካ ጦርነቱ እንዲቆም የተለያዩ ጫናዎችን ያደረገች ሲሆን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል በሚል የተለያዩ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች፡፡
በዋሸንግተን ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል በኢትዮጵያ ላይ ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ ማዕቀብ የሚባል ሲሆን በፈረንጆቹ መስከረም 2021 ላይ ለሁለት ዓመት የሚቆይ ማዕቀብ ተጥሏል፡፡
ይህ ማዕቀብ ከአንድ ሳምንት በኋላ የሚጠናቀቅ ቢሆንም ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ማዕቀቡ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲራዘም መፈረማቸውን አስታውቀዋል፡፡
አሜሪካ ማዕቀቡን ለአንድ ዓመት ያራዘመችው በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አሁንም ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ለምስራቅ አፍሪካ እና ለአሜሪካ የውጭ ጉዳዮች ፖሊሲ ስጋት ነው በሚል ነው፡፡
አሜሪካ ኢትዮጵያን ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚ ሀገርነት ዝርዝር ውስጥ ሰረዘች
የዓለማችን ባለግዙፍ ኢኮኖሚ የሖነችው አሜሪካ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚጎዳ ክስተት በየትኛውም ሀገር ሲከሰት ጥቅሟን ለማስከበር ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ ትግበራ የተሰኘ ፖሊሲ ያላት ሲሆን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በቀጥታ ውሳኔዎችን እንዲወስኑ ይፈቅዳል፡፡
ፖሬዝዳንት ባይደንም በዚህ ፖሊሲ መሰረት በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን እንዲጣል በቀጥታ ውሳኔዎችን ያሳለፉ ሲሆን ከአግዋ መሰረዝን ጨምሮ የተለያዩ የገንዘብ እና የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን ጥለዋል፡፡
ኢትዮጵያ እስካሁን በአሜሪካ አዲስ እርምጃ ዙሪያ ምላሽ ያልሰጠች ሲሆን የአግዋ እገዳ እንዲነሳ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆኗን ከዚህ በፊት በተሰጡ መግለጫዎች ላይ ተገልጿል፡፡