ሒላሪ ክሊንተን በ2016 ምርጫ ወቅት ለረጅም ወራት ተመራጯ እጩ ሆነው ቆይተው ነበር
ዶናልድ ትራምፕ በቀጣዩ ምርጫ ከጆ ባይደን የተሻለ ተመራጭ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
የዓለም ልዕለ ሀያሏ ሀገር አሜሪካ በሚቀጥለው ዓመት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫዋን እንደምታካሂድ ይጠበቃል፡፡
ሁለቱ የሀገሪቱ ጉምቱ ፓርቲዎች ዲሞክራቶች እና ሪፐብሊካን እጩ ፕሬዝዳናታቸውን በማሳወቅ ላይ ሲሆኑ እጩዎች የምረጡኝ ዘመቻቸውን ከወዲሁ በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ሌሎችም በቀጣዩ ምርጫ ላይ እንደሚወዳደሩም ገልጸዋል፡፡
ሲኤንኤን ይህን ምርጫ አስመልክቶ የተሻለ የህዝብ ተወዳጅነት ያለው እጩ ፕሬዝዳንት ማን ነው ሲል ያስጠናውን ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህ ጥናት መሰረት 36 በመቶ አሜሪካዊያን ከጆ ባይደን እና ዶናልድ ትራምፕ ውጪ አዲስ ፕሬዝዳንት ማየት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በስልጣን ላይ ካሉት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በአንጻራዊነት የተሻለ የሕዝብ ተመራጭነት እድል እንዳላቸው በጥናቱ ለይ ተጠቅሷል፡፡
በሲኤንኤን ጥናት ላይ ከተሳተፉ አሜሪካዊያን መካከል 32 በመቶ ያህሉ ጆ ባይደንን እንደሚመርጡ ሲናገሩ 33 በመቶዎቹ ደግሞ ዶናልድ ትራምፕን እንመርጣለን ብለዋል፡፡
እንዲሁም 31 በመቶዎቹ ደግሞ ከሁለት አንዳቸውን እንደሚመርጡ ተናግረዋል ተብሏል፡፡
ይሁንና ምርጫው እየተቃረበ ሲመጣ እጩዎቹ በሚያደርጓቸው የሀሳብ ክርክር በኋላ መራጮች ውሳኔያቸውን እንደሚቀይሩ አልያም እንደሚያጸኑ ይጠበቃል፡፡
በፈረንጆቹ 2016 በተካሄደው የአሜሪካ አጓጊ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሂላሪ ክሊንተን ለረጅም ጊዜ በአሜሪካዊያን ተወዳጅ እጩ ሆነው የዘለቁ ቢሆንም በመጨረሻ ተሸንፈዋል፡፡