
አብዛኛው በበሽታው የተያዙ ሰዎች ከሀገር ውጭ በሚጓዙበት ጊዜ እንደተያዙ ተገልጿል
በአሜሪካ በፍሎሪዳ እና ቴክሳስ ግዛት አምስት ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸው ተረጋግጧል።
ገዳይ የሆነ የወባ ተላላፊ በሽታ በአሜሪካ ሲገኝ በ20 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የሀገሪቱ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) አስታውቋል።
በፍሎሪዳ አራት ሰዎች፣ በቴክሳስ ደግሞ አንድ ሰው በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ በበሽታው መያዛቸው በምርመራ መረጋገጡን ማዕከሉ ገልጿል።
ሲዲሲ ባወጣው ማስጠንቀቂያ የወባ በሽታ እንደ ድንገተኛ ህክምና ተደርጎ እንደሚወሰድ እና ማንኛውም ምልክቱ ያለበት ሰው "በአስቸኳይ መታየት አለበት" ብሏል።
የፍሎሪዳ ግዛት የወባ በሽታ ማሳሰቢያ የሰጠ ሲሆን፤ ነዋሪዎቹ የቆዩ የውሃ ገንዳዎችን እንዲያፈሱ፣ የመስኮቶቻቸው ቀዳዳ እንደሌላቸው ማረጋገጥ እና ትንኞችን ለመከላከል ጸረ-ተባይ ኬሚካሎችን እንዲጠቀሙ አሳስቧል።
ይሁን እንጂ ሲዲሲ በአሜሪካ የወባ በሽታ የመከሰቱ እድል ዝቅተኛ እንደሆነ እና አብዛኛው በበሽታው የተያዙ ሰዎች ከሀገር ውጭ በሚጓዙበት ጊዜ እንደተያዙ ገልጿል።
95 በመቶው የወባ በሽታ በአፍሪካ እንደሚገኝ የጤና ኤጀንሲው ተነግሯል።
የወባ በሽታ የሚከሰተው በተወሰኑ ሴት ትንኞች በተሸከሙት አምስት ዝርያዎች ነው።
ምልክቶቹ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ራስ ምታት፣ የጡንቻ ህመም እና ድካም ናቸው። ማቅለሽለሽ፣ ተቅማጥ እና ማስታወክም ሊታዩ ይችላሉ።