የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ “ሩሲያ ቤላሩስን በቀጥታ ወደዚህ ጦርነት ለመሳብ እየሞከረች ነው” ብለዋል
ከቤላሩስ ወታደሮች ጋር አዲስ የተቀናጀ ጦር ኃይል ይፈጥራሉ የተባሉት የመጀመሪያዎቹ የሩሲያ ወታደሮች ቤላሩስ መግባታቸውን የሚንስክ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የጋራ ወታደራዊ ኃይል ተልዕኮ "የድንበርን ለማጠናከር ብቻ ነው" እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
ወታደሮቹ ቤላሩስ ሲደርሱ ባህላዊ አልባሳት ለብሰው ዳቦና ጨው የሚያቀርቡ ሴቶች አቀባበል ሲያደርጉላቸውም ነው በሚኒስቴሩ በኩል የተለቀቁ ምስሎች የሚያሳዩት፡፡
የፑቲን የቅርብ ወዳጅ የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ “ዩክሬን በእኛ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጀች ነው” ሲሉ ከቃናት በፊት መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
በተጨማሪም ሉካሼንኮ ፖላንድን፣ ሊትዌኒያን እና ዩክሬንን የቤላሩስ አክራሪዎችን “የሽብር ጥቃቶችን ለመፈጸም እና በሀገሪቱ ውስጥ ወታደራዊ ጥቃትን ለማደራጀት” የሚያስችል ስልጠና እየሰጡ ነው ሲሉ ከሰዋል፡፡
ሉካሼንኮ ከሀገሪቱ የደህንነት ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ስብሰባ "ዛሬ ዩክሬን እየተወያየች ብቻ ሳይሆን በቤላሩስ ግዛት ላይ ጥቃት ለማድረስ እቅድ እንዳላት አስቀድሜ ተናግሬያለሁ" ማለታቸውም ነው ቤልታ የተሰኘው የመንግስት የዜና ወኪል የዘገበው።
የሩሲያ ፌዴሬሽን እና የቤላሩስ ሪፐብሊክ ጥምር ጦር ለማሰማራት ከስምምነት መድረሳቸውም ተናግረው ነበር፡፡
እናም የአሁኑ የቤላሩስና የሩሲያ የጋራ ወታደራዊ ኃይል በዩክሬን ያለው ሁኔታ ይበልጥ እንዳያባብሰው ተሰግቷል ሲል ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በቡድን-7 ጉባኤ ላይ ባሰሙት ንግግር “ሩሲያ ቤላሩስን በቀጥታ ወደዚህ ጦርነት ለመሳብ እየሞከረች ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በዩክሬን-ቤላሩስ ድንበር ላይ የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ተልዕኮ እንዲደረግም ጠይቀዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
የቀድሞዋ የሶቪየት ህብረት አባል ሀገር የነበረችው ቤላሩስ ከዩክሬን ጋር ባለው ጦርነት ከሩሲያ ጎን ከቆሙ ሀገራት መካከል ብቸኛዋ ናት፡፡
ከቤላሩስ ውጪ ሁሉም የቀድሞዎቹ የሶቪየት ህብረት አባል ሀገራት ከሩሲያ በተቃራኒ ወይም ከምዕራባዊያን ጎን ተሰልፈው የተለያዩ እርምጃዎችን የወሰዱ ሲሆን የምዕራባዊያንን ማዕቀብ በማስፈጸም ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ፕሬዝዳንት ሉካሼንኮ ሞስኮ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከመጀመሯ በፊት በነበሩት ወራት ውስጥ በወታደራዊ ልምምድ ሰበብ የሩሲያ ወታደሮችን ወደ ቤላሩስ እንዲገቡ የፈቀዱ መሪ ናቸው፡፡
ከጦርነቱ በኋላም ቢሆን በሩሲያ ላይ የሚቃጣ የትኛውንም ጥቃት ቤለሩስ እንደምትመክትና እንደምትከላከል በአደባባይ በመናገር ለፑቲን ያላቸው አጋርነት ያረጋገጡባቸው በርካታ አጋጠሚዎች ይታወሳሉ፡፡