አሜሪካ የኢትዮጵያ ጦርነት ተሳታፊዎች ግጭቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ጠየቀች
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሜሪካ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ለሚደረገው የስላም ሂደት እንደምትደግፍም ገልጸዋል
ብሊንከን፤ መንግስትም ሆነ ህወሓት ጦርነቱ እንዲያበቃ የሰላም መንገድን መከተል ያለባቸው አሁን ነው ብለዋል
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ አካላት ግጭቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ጠየቁ፡፡
የከሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን በትዊተር ገጻቸው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት በትግራይ ውስጥ የሚያካሂዱትን “የጋራ ወታደራዊ ጥቃት” ሊያቆሙ ይገባል ብለዋል።
በተጨማሪም የህወሓት ባለስልጣናት “ከጠብ አጫሪነት ተግባራትን” እንዲቆጠቡ ብሊንከን አሳስበዋል፡፡
ብሊንከን የኢትዮጵያ መንግስት እና የህወሓት ባለስልጣናት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲያበቃ የሰላም መንገድን መከተል ያለባቸው አሁን ነው ብለዋል።
አሜሪካ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ለሚደረገው የስላም ሂደት እንደምትደግፍም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡
ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ሳምናት በቀሩት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ የተደረገው የተኩስ አቁም ነሀሴ ላይ ተደናቅፎ ጦርነት ከጀመረ በኋላ ውጊያዎች እየተካሄዱ የተለያዩ መረጃዎች በመውጣት ላይ ናቸው፡፡
ከሁለት ሳምንታት በፊት በደቡብ አፍሪካ እንዲካሄድ በአፍሪካ በኩል የተያዘው መርሃ-ግብርም ቢሆን የሎጂስቲክ ችግር በሚል ምክንያት በራዘሙ የሚታወስ ነው፡፡
የአሜሪካው ለፍተኛ ዲፕሎማት አምባሳደር ማይክ ሐመር በትናንትናው እለት ከኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደምቀ መኮንን ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት በድርድር እንዲፈታ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡
ልዩ መልእክተኛው ማይክ ሐመር በአሁኑ ጉዞዋቸው ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ወደ ናይሮቢ እና በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በማቅናት በኢትዮጵያና እና በምስራቅ አፍሪካ ጉዳይ ከሀገራቱ ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል።
ልዩ መልእክተኛው ማይክ ሐመር ባለፈው ነሃሴ ድጋሚ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ለማስቆም እና ድርድር እንዲጀመር ለማበረታታት አዲስ አበባ ሰንብተው ወደ ዋሽንግተን መመለሳቸው የሚታወስ ነው።
ማይክ ሐመርወደ አሜሪካ ከተመለሱ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ፤ ህወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል ያለውን ግጭት ለማስቆም ዋነኛ እንቅፋት የሆነው “በሁለቱም ወገኖች በኩል ያለው አለመተማመን ነው” ማለታቸው አይዘነጋም።
ጉዳዩ አሳሳቢ ቢሆንም ግን “የድርድር ተስፋ አለ”ም ነበር ያሉት ማይክ ሐመር፡፡
አሪካ፣አውስትራሊያ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድስ እና ብሪታኒያ ከቀናት በፊት ባወጡት መግለጫ ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት እንዲቆም መጠየቃቸው አይዘነጋም፡፡
“የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ወታደራዊ ግጭትን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ፣ ጦርነቱ እንዲቆም ስምምነት እንዲደረግ፣ ያልተገደብ ሰብዓዊ አገልግሎት እንዲሰጥ እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት መሪነት ሰላማዊ ድርድር እንዲካሄድ እንጠይቃለን” ብለዋል ሀገራቱ በመግለጫቸው፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣውን የኤርትራ ወታደራዊ ሃይሎች ተሳትፎም እንደሚያወግዙ የገለጹት ሀገራቱ፤ የኤርትራ ኃይሎች ወታደራዊ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያቆሙም ጠይቀዋል፡፡
ሁሉም የውጭ ተዋናዮች ይህንን ግጭት የሚያባብሱ ድርጊቶችን ማቆም አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል፡፡