የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ከጆ ባይደን ጋር መነጋገሩ “አስፈላጊነቱ ብዙም አይታየኝም ” አሉ
ፕሬዝዳንት ባይደን ከፑቲን ጋር ብዙም የመገናኘት ፍላጎት እንደሌላቸው በዚህ ሳምንት መናገራቸው አይዘነጋም
የዩክሬን ጦርነት በባይደን እና ፑቲን መካከል የነበረውን ግንኙነት እንዲሻክር ምክንያት መሆኑ ይነገራል
በዩክሬን ጦርንት ምክንያት ከአሜሪካ መሪዎች ጋር ያለቸው ግንኙነት እየሻከረ የመጣው የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከባይደን ጋር መነጋገሩ “አስፈላጊነቱ ብዙም አይታየኝም ” አሉ፡፡
ፑቲን ይህን ያሉት በመጪው ወርሃ ህዳር በኢንዶኔዥያ በሚኖረው የቡድን-20 ሀገራት ጉባኤ ላይ ከአሜሪካው ኣቻቸው በጎንዮሽ ይገናኛሉ..? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምልሽ ነው፡፡
በዚህም መሰረት ፐሬዝዳንቱ "ከእኔ ጋር እንደዚህ አይነት ንግግር ለማድረግ ጆ-ባይደን ራሳቸው ዝግጁ ናቸው ወይስ አይደሉም ብለን ልንጠይቃቸው ይገባል፤ እውነቱን ለመናገር ግን አስፈላጊነቱ ብዙም አይታየኝም " የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በኢንዶኔዥያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ የሚኖራቸው ተሳትፎ እስካሁን አልተወሰነም ሲሉ መናገራቸውም ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
ቭላድሚር ፑቲን በካዛክስታን የተካሄደውን ስብሰባ ተከትሎ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "ወደዚያ የመጓዜ ነገር ገና አልተወሰንም፤ ነገር ግን ሩሲያ በእርግጠኝነት ትሳተፋለች ፤ እያሰብንበት ነው"ም ብለዋል፡፡
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ባይደን ከፑቲን ጋር ብዙም የመገናኘት ፍላጎት እንደሌላቸው መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ሞስኮ በዩክሬን ላይ የጀመረችው ወታደራዊ ዘመቻን ተከትሎ አሜሪካም ሆነ ምዕራባውያን በክሬምሊን ባለስልጣናት ድርጊት ኩፉኛ መቆጣታቸው የሚታወቅ ነው፡፡
በዋሽንግተን እና ሞስኮ ባለስልጣናት በተለይም በጆ-ባይደንና ፑቲን መካከል የነበረው ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱም ይነገራል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በአንድ ወቅት ወደ ፖላንድ ተጉዞው የዩክሬን ተፈናቃዮችን መጎብኘታቸው ተከትሎ በፑቲን ላይ የሰነዘሩት ጠንከር ያለ ዘለፋና ማስጠንቀቅያ እጅግ አስገራሚ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በተፈናቃዮቹ ሁኔታ ውስጣቸው ኩፉኛ ያዘነው ጆ-ባይደን ፑቲን “ፑቲን ገዳይና የጦር ወንጀለኛ ነው” ስለዚህም በስልጣን መቆየት አይችልም ያሉበት አጋጣሚ የሩሲያ ባልስልጣናትን ያስቆጣ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ሩሲያ በወቅቱ በሰጠችው ምላሽ መግፕሬዘዳንት ባይደን የተናገሩትን ንግግር “ተቀባይነት የሌለና መቸም ይቅር የማይባል ነው” ማላቷም የሚታወቅ ነው፡፡
በዚህም የሁለቱም ኃያላን ሀገራት መሪዎች አሁን ድረስ እንደሻከረ መሆኑንና ምናልባትም ዩክሬንን ሽፋን ያደረገው ውጥረት ሀገራቱን ወዳልተፈለገ ግጭት እንዳይወስዳቸው ተሰግቷል፡፡