ተመድ “የሰላም ጥረቶች በቁም ነገር ካልተያዙ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው፣ መቁሰላቸው እና መፈናቀላቸው ይቀጥላል” አለ
ፍሊፖ ግራንዲ “የሰብዓዊ ርዳታ ሰራተኞች ያለስጋት ስራቸውን መስራት መቻል አለባቸው”ም ብለዋል
ፍሊፖ ግራንዲ “የሰብዓዊ ርዳታ ሰራተኞች ያለስጋት ስራቸውን መስራት መቻል አለባቸው”ም ብለዋል
በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት እንዲያበቃ የሚደረጉ የሰላም ጥረቶች በቁም ነገር ካልተያዙ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው፣ መቁሰላቸው እና መፈናቀላቸው ይቀጥላል ሲሉ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር (ዩኤንኤችሲአር) ፍሊፖ ግራንዲ ተናገሩ፡፡
ኮሚሽነሩ በትዊተር ገጻቸው በሳፈሩት ጽሁፍ “የሰብዓዊ ርዳታ ሰራተኞች ኢትዮጵያውያንን እና የነፍስ አድን ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ስደተኞችን ለመርዳት በሚያደርጉት ጥረት ያለስጋት ስራቸውን መስራት መቻል አለባቸው”ም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ኔቨን ክሬቨንኮቪች ዳግም ባገረሸው ጦርነት ምክንያት በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ለሚገኙ ተፈናቃዮች በሚፈለገው ደረጃ እርዳታ ማዳረስ እንዳልተቻለ በቅርቡ ለአል-ዐይን አማርኛ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
በተጨማሪም በትግራይ ማይ ዓይኒ እና ዓዲ ሓሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ 10 ሺህ የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች ይሰጥ የነበረው የሰብዓዊ እርዳታ መቋረጡ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ወደ ትግራይ ሲደረግ የነበረው የተመድ የሰብአዊ አየር አገልግሎት በረራ በመቆሙ ምክንያት በግጭቱ ለተጎዱ ዜጎችና ኤርትራውያን ስደተኞች የህይወት አድን እርዳታ የሚሰጡ የዩኤንኤችሲአርን ጨምሮ ሌሎች ግብረሰናይ ሰራተኞች ወደ ትግራይ ክልል መግባት ባለመቻላቸውና የጥሬ ገንዘብ እቅረቦት ባለመኖሩ ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
ቃል አቀባዩ በአማራ ክልል ዳባት አለምዋጭ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ስለሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ሁኔታ ሲገልጹም፤ ከዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ የሚደረገው ድጋፍ በቂ እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡
ከተጀመረ ሁለት አመት ሊሞላው ሁለት ሳምታት ብቻ የቀሩት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በተለይም በትግራይ ክልል በነበሩት የኤርትራ ስደተኞች ላይ ያስከተለው ጉዳትና እንግልት ከባድ እንደሆነ የተመድ መረጃ ያመለክታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ጦርነቱን ተከትሎ ወደ ከተማ የሚገቡ የስደተኞችን ቁጥር “በእጅጉ እንዲያሻቅብ” ማድረጉን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
በኢትዮጵያ የድርጅቱ ተወካይ ማማዱ ዲያን (ዶ/ር) በተፈጠረው የጸጥታ ቀውስ ምክንያት ከተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ሸሽተው የመጡ በርካታ ስደተኞች በአዲስ አበባ እንደሚገኙ በቅረቡ ለአል-ዐይን አማርኛ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ከተማ 30 ሺህ የነበረው የስደተኞች ቁጥር አሁን ላይ 80 ሺህ መድረሱንም የድርጅቱ ተወካይ ተናግረዋል።
ከየመጠለያ ጣቢያዎቹ ከሸሹት ስደተኞች መካከል በርካቶቹ ኤርትራውያን መሆናቸውም ነበር የገለጹት ተወካዩ፡፡