የፍሬንድስ ሲትኮም ተወናይ ማቲው ፔሪ ሞት ጋር በተገናኝ 5 ሰዎች ተከሰሱ
የግል ሀኪሙን እና ረዳቱን ጨምሮ አምስት ሰዎች በተዋናዩ አሟሟት ላይ እጃቸው እንዳለበት ተነግሯል
ግለሰቦቹ ጥፋተኛ መሆናቸው ከተረጋገጠ ከ10 – 25 አመት ጽኑ እስራት ይጠብቃቸዋል
የፍሬንድስ ሲትኮም ተወናይ ማቲው ፔሪ ሞት ጋር በተገናኝ 5 ሰዎች ተከሰሱ።
ፍሬንድስ የተሰኝው በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅነትን ያገኘው አስቂኝ ተከታታይ ድራማ ተዋናዩ ማቲው ፔሪ ሞት ጋር በተገናኝ አምስት ሰዎች መከሰሳቸው ታውቋል።
ማቲው ፔሪ ከ 10 ወራት በፊት ነበር ኬታሚን የተሰኘ ለድብርት እና ለጭንቀት የሚወሰድ መድሀኒት ከመጠን በላይ በመጠቀም በሎስአንጀለስ በሚገኘው ቤቱ በመታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ሞቶ የተገኝው፡፡
ከ10 ወራት ምርመራ በኋላ ፖሊስ ይፋ ባደረገው መረጃ ከተዋናዩ ግድያ ጋር በተገናኘ የግል ረዳቱ እና ሀኪሙን ጨምሮ አምስት ግለሰቦች እጃቸው እንዳለበት አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ኬታሚን የተሰኝው መድሀኒት በድብርት እና በጭንቀት ውስጥ ለሚገኙ እንዲሁም በቀዶ ጥገና ወቅት ለስቃይ ማስታገሻ የሚወሰድ መድሀኒት ነው፡፡
ባለፉት አመታት በከባድ የመጠጥ እና መድሀኒት የሱስ ችግር ውስጥ የነበረው የ54 አመቱ ተዋናይ ከ2001 ጀምሮ ከሱስ ነጻ መሆኑ ቢነገርም በሀኪሞች የታዘዘለትን ኬታሚን የተሰኘውን መድሀኒት ይወስድ እንደነበር ተነግሯል፡፡
የግል ሀኪሙ እና ረዳቱ ተወናዩ ለአመታት ከሱስ ጋር የነበረበትን ትግል እንደአጋጣሚ በመጠቀም ዶክተሩ ከፍተኛ መጠን ያለው መድሀኒት ሲያዝለት ረዳቱ ደግሞ በህገወጥ መንገድ መድሀኒቱን እየገዛ ያቀርብ እንደነበር ፖሊስ ባደረገው ማጣራት ደርሶበታል፡፡
ማቲው ፔሪ ሞቶ በተገኘበት ወቅትም የግል ረዳቱ መድሀኒቱን ወግቶት እንደነበር ታውቋል፡፡
ፖሊስ ረዳቱ እና የግል ሀኪሙ በመመሳጠር እያደረጉት የነበረው ነገር የተዋናዩን የመድሀኒት ፍላጎት የሚጨምር እና ቀስበቀስም የሚጎዳው እንደሆነ እያወቁ ሆን ብለው አድረገውታል ሲል መረጃውን አጠናክሯል፡፡
የግል ሀኪሙ በየጊዜው የሚያዝለት ከፍተኛ መጠን ያለው መድሀኒት ሱስ ውስጥ የከተተው ተዋናዩ በህጋዊ በመድሀኒት ቤቶች ከተፈቀደለት መጠን በላይ ማግኝት ባለመቻሉ በህገወጥ መንገድ መድሀኒቱን ወደ መሸመት ተሸጋግሯል ነው ያለው፡፡
በዚህም “የኬታሚኗ ንግስት” በሚል ቅጽል ስም ከምትታወቀው የመድሀኒቱ አቅራቢ ጋር ሁለቱ ግለሰቦች የጥቅም ትስስር መስርተው እንደነበርም ተደርሶባቸዋል፡፡
ማቲው ከሞሞቱ ሁለት ወራት በፊትም 55ሺህ ዶላር የሚወጣ የኬታሚን መድሀኒት ከግለሰቧ የግል ረዳቱ ግዢ ስለመፈጸሙም ነው የተነገረው፡፡
የግል ሀኪሙ እና ረዳቱን ጨምሮ ሶስት ሰዎች ጥፋተኛ መሆናቸውን ያመኑ ሲሆን በሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ላይ ፖሊስ መረጃዎችን ማሰባሰብ መቀጠሉ ተሰምቷል፡፡
ግለሰቦቹ ጥፋተኛ መሆናቸው ከተረጋገጠ በወንጀሉ ላይ እንዳላቸው ድርሻ ከ10 እስከ 25 አመት እስር ሊፈረድባቸው ይችላል፡፡
ማቲው ፔሪ በተከታታይ አስቂኝ ድራማዎች ታሪክ ውስጥ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዝና እና ተቀባይነት ባገኘው “ፍሬንድስ” ፊልም “ቻንድለር” የተሰኝ ገጸባህሪ በመጫወት አድናቆትን አግኝቷል፡፡
ከ1994 – 2004 በ10 ምዕራፎች ተከፍሎ ለአስር አመታት ለዕይታ የበቃው “ፍሬንድስ” የመጨረሻውን ክፍል ብቻ 52 ሚሊየን ሰዎች ተመልክተውታል፡፡