ሩሲያ በኩርስክ ግዛት የኔቶ መሳሪያዎችን የታጠቀ የወደታሮች ቡድን ደመሰስኩ አለች
የደህንነት ባለስልጣኑ እንደገለጹት ሩሲያ ስዊድን እና አሜሪካ ሰራሽ መሳሪያዎችን ይዛለች
ፕሬዝደንት ፑቲን "አደጋኛ ትንኮሳ" ሲሉ የጠሩትን ይህን ጥቃት እንዲመክት ለሩሲያ ጦር ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል
ሩሲያ በኩርስክ ግዛት የኔቶ መሳሪያዎችን የታጠቀ የወደታሮች ቡድን ደመሰስኩ አለች።
የሩሲያ ኃይሎች የኔቶ ሀገራት መሳሪያዎችን የታጠቁ የቅኝት እና የአሻጥረኞች ቡድንን በኩርስክ ግዛት መደምሰሳቸውን ሮይተርስ የሩሲያውን ሪያ የዜና አገልግሎትን ጠቅሶ ዘግቧል።
"በአሜሪካ እና በስዊድን የተመረቱ የጦር መሳሪያ ናሙናዎችን የዩክሬን የአሻጥር ቡድን መሽጎ በነበረበት ክሬምያኖይ መንደር አቅራቢያ" መገኘቱን ሪያ የሩሲያ የደህንነት ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
የደህንነት ባለስልጣኑ እንደገለጹት ሩሲያ ስዊድን ሰራሽ አውቶማቲክ ካርቢን-5 ጠብመንጃ እንዲሁም አሜሪካ ሰራሽ ኤም-4 ጠብመንጃ እና አም2 መትረጌስ ይዛለች።
ሩሲያ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት በኩርስክ ግዛት ድንበሯን ጥሰው ከገቡ የዩክሬይን ወታደሮች ጋር እየተዋጋች ትገኛለች።
ሩሲያ ከኩርስክ ግዛት ወረራ የፈጸሙትን የዩክሬን ወታደሮች ለማስወጣት የተወሰነ ኃይል በዩክሬን ከያዘቻቸው ግዛቶች እያስወጣች ነው የሚሉ መረጃዎች ወጥተዋል።
ዩክሬን ከሩሲያ ሉአላዊ ግዛት አንድ ሺ ስኩየር ኪሎሜትር ስፋት ያለው ቦታ መያዟን አስታውቃለች። አንድ ሳምንት ባስቆጠረው በዚህ ጥቃት ከ200ሺ በላይ ሩሲያውያን ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን በንጹሃን እና በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል ተብሏል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የዩክሬን ወታሮች በሩሲያ ግዛት ውስጥ ጥቃት መክፈታቸው ይፋ ከሆነ በኋላ ባደረጉት ንግግር ስለጉዳዩ በቀጥታ ባይጠቅሱም "የዩክሬን ወታደሮች እንዴት ማስደንገጥ እንዳለባቸው ያውቃሉ" ሲሉ ለ አድናቆታቸውን ገልጸውላቸዋል።
ፕሬዝደንት ፑቲን "አደጋኛ ትንኮሳ" ሲሉ የጠሩትን ይህን ጥቃት እንዲመክት ለሩሲያ ጦር ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል።