ሩሲያ ድንበሯን ጥሶ የገባውን ጦር ለመከላከል ከዩክሬን ግዛቶች ወታደሮቿን እያስወጣች እንደምትገኝ ተገለጸ
የዩክሬን ጦር በምዕራባዊ ሩሲያ ኩርሰክ ግዛት ካላፈው ሳምንት ጀምሮ ጥቃት መሰንዘሩ ይታወሳል
ሩሲያ እስካሁን ድረስ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው ወታደሮቿን በስፍራው ማሰማራት አልጀመረችም ነው የተባለው
ሩሲያ ድንበሯን ጥሶ የገባውን ጦር ለመከላከል ከዩክሬን ግዛቶች ወታደሮቿን እያስወጣች እንደምትገኝ ተገለጸ።
ሩሲያ ድንበሯን ጥሶ የገባውን የዩክሬን ጦር ለመከላከል በሰሜናዊ ዩክሬን በቁጥጥሯ ስር ከሚገኙ አካባቢዎች ወታደሮቿን እያሰወጣች መሆኑ ተሰምቷል፡፡
ሲኤን ኤን የአሜሪካ የደህንነት መስሪያ ቤት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንዳስነበበው እስካሁን ቁጥራቸው አንድ ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች ከዩክሬን ወደ ሩሲያ ምእራባዊ ግዛት ተዘዋውረዋል፡፡
ዩክሬን ከባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጀምሮ በሩሲያ በፈጸመችው ወረራ ከ200 ሺህ በላይ ሩሲያውያን ተፈናቅለዋል፤ ለሳምንት በቀጠለው ውጊያም በንጹሃን ህይወትና ንብረት ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱ ነው ሲዘገብ የቆየው።
ኬቭ ከሩሲያ ግዛት ውስጥ ከ1ሺህ ስኩየር ኪሎሜትር በላይ መሬት መቆጣጠሯን ማስታወቋም ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ ሩሲያ ጦሩን ከግዛቷ ለማስወጣት በከባድ መሳርያ የታገዘ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ በመወሰድ ላይ ስትሆን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን የዩክሬን ጦር ወደ ፊት እየገፋ እንደሚገኝ በመዘገብ ላይ ናቸው፡፡
የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ በአሁኑ ወቅት ሩሲያ ከፍተኛ የሜካናይዝድ ብርጌዶችን ጨምሮ በሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ከሰሜናዊ ዩክሬን በማስወጣት ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡
ቃል አቀባዩ አክለውም ሩሲያ ምንም እንኳን ወደ ኩርስክ ግዛት ወታደሮቿን እያዘዋወረች ቢሆንም በሰሜን ምስራቅ በደቡብ ዛፖሪዚያ ወደ ፊት ለመግፋት እያደረገች ያለውን ውግያ ቀጥላለች ነው ያሉት፡፡
ዩክሬን በሩሲያ ግዛት ውስጥ ዘልቆ በመግባት እየፈጸመች ያለችው ጥቃት የሚቆይበት ጊዜ የጦርነቱ ስትራቴጂካዊ ውጤት ላይ የሚፈጥረውን ተጽእኖ እንደሚወስነው ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ዩክሬን በኩርሰክ ግዛት የፈጸመችው ጥቃት ውግያው ከሚገኝበት አንድሺ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ግዛቷን የመከላከል አቅም ሊያሳሳው እንደሚችል ነው የተነገረው፡፡
የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ እንደተናገሩት ዩክሬን የፈጸመችው ድንገተኛ ጥቃት ሩሲያ የሀይል መከፋፈል እና ወጥ ስትራቴጂ እንዳይኖራት በማድረጉ በኩል አስተወጽኦ ሊኖረው ይችላል፡፡
በዩክሬን ግዛት ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ያሏት ሩሲያ አንድ ሺህ ወታደሮችን ማስወጣቷ በአጭር ጊዜ ውስጥ በጦርነቱ ሂደት ላይ ለውጥ ባይኖረውም በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና በወታደራዊ አመራሮቻቸው ላይ የሚፈጥረው ጫና ግን ቀላል የማይባል ነው ተብሏል፡፡
በኩርስክ ግዛት የብዙ አመታት ልምድ ያላቸውን ወታደሮቿን እስካሁን ማሰማራት አለመጀመሯን ሲኤንኤን ያነጋገራቸው ሌላ የአውሮፓ ህብረት የደህንነት ባለሙያ ተናግረዋል፡፡
ምዕራባውያን ሀገራት ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ ዩክሬን የሩሲያን ድንበር ጥሶ በመግባት ከፈጸመችው ጥቃት ጀርባ እጃቸው እንደሌለበት ቢናገሩም ውሳኔውን እንደሚደግፉት ገልጸዋል፡፡
አሜሪካ እስካሁን ለዩክሬን የሰጠቻቸውን የረጀም ርቀት ተመዝግዛጊ ሮኬቶች በኩርሰክ ግዛት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቃድ አለሰጠችም፡፡
ብሪታንያ በበኩሏ ለዩክሬን የላከቻቸው የጦር መሳሪያዎች በሩሲያ ግዛት ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቅዳለች።
የሩሲያን ድንበር ጥሶ የገባው የዩክሬን ጦር "ቻሌንጀር 2 " የተሰኘውን የብሪታንያ ታንክ እየተጠቀመ እንደሚገኝ ተዘግቧል።