በጃፓን እየተስፋፋ የሚገኘው የሰው ስጋ የሚመገበው ባክቴሪያ
በሁለት ሰአታት ውስጥ በሚገድለው በሽታ እስካሁን 944 ሰዎች ሲያዙ 77ቱ ህይወታቸው አልፏል
በሽታው ከ1999 ጀምሮ መታየት የጀመረ ሲሆን በባለፈው አመት ከጃፓን በተጨማሪ በ5 የአውሮፓ ሀገራት ላይ ታይቷል
የሰው ስጋ የሚመገበው ባክቴሪያ ኢንፌክሽን ስርጭት በመጨመር ላይ እንደሚገኝ የጃፓን የጤና ባለስልጣናት አስታወቁ፡፡
ኤስቲኤስኤስ የተሰኝው ባክቴሪያ አደገኛ እና ገዳይ ኢንፌክሽን የሚፈጥር ሲሆን የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩ ሰዎች በቶሎ ህክምና ካላገኙ በ48 ሰአታት ውስጥ ህይወታቸው እንደሚያልፍ ነው የተነገረው፡፡
በደም መተላለፍያ ውስጥ በሚሰራጩ ባክቴሪያዎች የሚፈጠረው በሽታ ከፍተኛ ትኩሳት ፣ ማስታወክ እና የጡንቻ ህመም ምልክቶቹ ሲሆኑ በቶሎ ካልታከመ የሰውነት አካላት ስራቸውን እንዲያቆሙ በማድረግ በአፋጣኝ ይገድላል ነው የተባለው፡፡
በበሽታው ከሚያዙ 10 ሰዎች ሶስቱ የሚሞቱ ሲሆን በቅርብ አመታት በጃፓን እየታየ ያለው የባክቴሪያው ስርጭት አስጊ ደረጃ መድረሱን ሲኤንኤን አስነብቧል፡፡
ባክቴሪያው ከሰውነት ቆዳ ጋር በሚኖር ንክኪ እና በጉሮሮ በኩል በምግብ እና በተለያዩ መንገዶች ወደ ሰውነት የሚገባ ስለመሆኑ የጤና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፣ በሰውነት ውስጥ በሚኖረው ቆይታም እጅ እና እግር አካባቢ የሚገኝውን የሰው ስጋ እንደሚመገብ ነው ባለሙያዎቹ የተናገሩት፡፡
ካንሰር እና ስኳርን የመሳሰሉ ተጓዳኝ በሽታዎች ያለባቸው ሰዎች በዚህ በሽታ የመያዝና የመሞት አድላቸው ከፍተኛ መሆኑም ተሰምቷል፡፡
ከፈረንጆቹ 1999 ጀምሮ በጃፓን መታየት የጀመረው ባክቴሪያ መንስኤው ምን እንደሆነ ሳይንቲስቶቹ ገና ባይደርሱበትም በሀገሪቱ ባለፈው አመት በሽታው ከነበረበት ስርጭት ሲያድግ የገዳይነት አቅሙም 30 በመቶ መጨመሩ ነው የተነገረው፡፡
በ2022፣ 5 የአውሮፓ ሀገራት ከ10 አመት በታች በሆኑ ህጻናት ላይ የበሽታው ምልክት መታየቱን ለአለም ጤና ድርጅት አመልክተው ነበር ፡፡
በ2023፣ 50 አመት እና ከዛ በላይ እድሜ ባላቸው ሰዎች ኤስቲኤስኤስ የተሰኝው ቫይረስ ስርጭት እያደገ መሆኑን ያስታወቁት የጃፓን የጤና ባለስልጣናት ዜጎች ምልክቶቹን በንቃት እንዲከታተሉ እና በቶሎ ወደ ጤና ተቋማት እንዲያመሩ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል፡፡
የቀዶ ጥገና ያደረጉ እና በሰውነታቸው ላይ ቁስል ያለባቸው ሰዎች ለበሽታው ተጋላጭ ሲሆኑ ወደ ሌሎች ሰዎች የማስተላለፍ አድላቸውም ከፍተኛ ነው ተብሏል