ሃጃጆች በጀመራት ጠጠር መወርወር ጀምረዋል
የሀጂ ተጓዦች በኢድ አል አድሃ የመጀመሪያው እለት ሰባት ጠጠሮችን ይወረውራሉ
የጀመራት ድልድይ በስአት 300 ሺህ ሃጃጆች የጠጠር ውርወራውን እንዲያካሂዱ በሚያስችል መልኩ ተሰርቷል
1445ኛው የኢድ አል አድሃ በዓል በመላው አለት እየተከበረ ነው።
በሳኡዲ አረቢያ ለሃጅ ስነስርአት ከመላው አለም የተሰባሰቡ ሙስሊሞች ካደሩበት ገላጣማ ስፍራ ሙዝዳሊፋህ ወደ ሚና እና መካ ተመልሰው በጀመራት ጠጠር መወርወር ጀምረዋል።
ሃጃጆች በሙዝዳሊፋህ የሰበሰቧቸውን ጠጠሮች በሶስት መወርወሪያ ስፍራዎች በመገኘት ይወረውራሉ።
የጠጠር መወርወር ስርአቱ ነብዩ ኢብራሂም ልጁን ኢስማኤል ለመሰዋት ሲዘጋጅ የአምላኩን ትዕዛዝ እንዳይፈጽም በሰይጣን ከመፈተኑ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይነገራል።
አንዳንዶች ጠጠር መወርወርን ሰይጣንን እንደ መደብደብ ወይም መውገር አድርገው በመቆጠር ከጠጠር አልፎ ድንጋይ እስከመወርወር መድረሳቸው ሃይማኖታዊ መሰረት እንደሌለው የእስልምና አባቶች ይገልጻሉ።
ስነስርአቱ ወርዋሪው ከእኩይ ድርጊቶች መራቁን የሚገልጽበት ተምሳሌት ተደርጎ ይወሰዳል።
ዛሬ የተጀመረው የጠጠር ውርወራ ሃጃጆች በታላቁ መስጂድ ካባን ዞረው ሃጂያቸው እስኪጠናቀቅ ድረስ ይቀጥላል።
1 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የጀመራት ድልድይም በስአት 300 ሺህ ሃጃጆች የጠጠር ውርወራውን እንዲያካሂዱ በሚያስችል መልኩ መሰራቱ ነው የተነገረው።
ሳኡዲ 28 አሳንስሮች እና 20 በሮች ያሉት የጠጠር መወርወሪያ ስፍራ በ2030 ስድስት ሚሊየን የሃጂ ተጓዦችን እንዲያስተናግድ በሚያስችል መልኩ መገንባቷንም ዘ ናሽናል ዘግቧል።
ማስፋፊያው በጠጠር ውርወራው ወቅት ከዚህ ቀደም በመረጋገጥ ይደርሱ የነበሩ ጉዳቶችን ለመቀነስ እንደሚያግዝ ተነግሯል።
በአካባቢው ያለው ሙቀት ከሰዎች ብዛት ጋር ተዳምሮ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቀነስም ጠጠር የሚወረውሩ ሃጃጆች በፍጥነት እንዲወጡ እየተደረገ ነው ተብሏል።