ለረጅም ጊዜ ቴሌቪዥን መመልከት የሚያስከትለው የጤና ተጽዕኖ ምንድን ነው?
ቴሌቪዢን ላይ ረጅም ጊዜ የሚያጠፉ ሰዎች እድሚያቸው በሚገፋ ወቅት የማሰላሰል እና ሰውነታቸውን የማዘዝ ችግር ያጋጥማቸዋል ተብሏል
በ2030 ከአለም አጠቃላይ ህዝብ 20 በመቶው እድሜው 65 እና ከዚያ በላይ ይሆናል
ሰዎች ለመዝናኛነት ሰፊ ጊዜያቸውን ከሚያሳለፉባቸው መንገዶች መካከል ቴሌቪዥን ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይሰለፋል፡፡
የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በቅርቡ ይፋ ያደረጉት ጥናት ረጅም ግዜ ቴሌቪዥን ላይ የሚያሳልፉ ሰዎች አድሜያቸው በሚገፋ ወቅት የተለያዩ የጤና እክሎች እንደሚገጥማቸው አመላክቷል፡፡
የማሰላሰል አቅም መቀነስ፣ ሰውነትን ለማዘዝ መቸገር እና ሌሎችም ስር የሰደዱ የጤና እክሎች ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ነው ጥናቱ የጠቀሰው፡፡
ሰዎች በኋለኛ የእድሜ ዘመናቸው የሚያጋጥሟቸው የጤና እክሎች በወጣትነት እድሜያቸው በሚከተሏቸው የህይወት ዘይቤዎች ይወሰናል ያለው ጥናቱ፤
የአመጋገብ ስርአት፣ አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ የአልኮል እና ሌሎች ሱሶች ተጋላጭነት እንዲሁም ለረጅም ግዜ ቴሌቪዥን መመልከት ከዚህ ውስጥ እንደሚካተት ነው የገለጸው፡፡
45ሺህ ቴሌቪዥን ለረጅም ሰአት በሚመለከቱ እና በማይመለከቱ ሰዎች መካከል የተደረገው ጥናት ቴሌቪዥን ላይ ሰፊ ግዜ በሚያጠፉት ሰዎች ላይ ጤናማ የእድሜ ኡደት በ12 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ ተነግሯል፡፡
ከዚህ ባለፈም ብዙ ጊዜ ቲቪ ላይ ተቀምጦ ማሳለፍ ወደ አእምሮ የሚሄደውን የደም ዝውውር ከማዛባቱም በላይ ሰዎች ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ስርአትን እንዲከተሉ ምክንያት ይሆናል ተብሏል።
የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ሰዎች በቀን ከሶስት ሰአት ያልበለጠ የቴሌቪዥን ቆይታ እንዲኖራቸው እና በቀን ውስጥ ቢያንስ ለሁለት ሰአት ቀለል ያለ የእርምጃ እንቅስቃሴን ቢያደርጉ ከእድሜ ጋር የሚመጡ በሽታዎችን መቋቋም እንደሚችሉ ያሳይል።
በተጨማሪም የተስተካከለ የእንቅልፍ ስነስርአትን መከተል ለጤናማ እርጅና ሌላው መሰረታዊ ነጥብ ነው ተብሏል፡፡
ምሽት ላይ ቲቪ ላይ የሚጠፋውን እንቅልፍ በመቀነስ የ8 ሰአት እንቅልፍ ለማግኝት መሞከር ጠዋት ላይ የተነቃቃ አዕምሮ እና ለስራ ዝግጁ የሆነ አካል እንዲኖር ያደረጋል ብሏል ጥናቱ፡፡
በ2030 ከአለም አጠቃላይ ህዝብ 20 በመቶ የሚሆነው አድሜው 65 እና ከዛ በላይ እንደሚሆን ሲነገር በዚህ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ከህይወት ዘይቤ (ላይፍ ስታይል) ጋር በተገናኘ በሚመጡ በሽታዎች ተጋላጭነት ሰፊ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡