የአፍሪካ ህብረት ታዘቢ ቡድን መሪ ክላሰው ኮሚሰሎም የማእከላዊ አፍሪካዊቷን ሀገር ምርጫ አወድሰዋል
የአፍሪካ ህብረት የቻድን ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ያወደሰው ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመካሄዱ መሆኑን የፈረንሳይ ዜና ወኪል/ኤ.ኤፍ.ፒ/ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ከምርጫው ጋር በተያያዘ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሰልፎች እንደታገዱ ፣ በኃይል እንደተበተኑ እንዲሁም ባለሥልጣናት ተቃዋሚዎችን በቁጥጥር ስር እንዳዋሉ የሚገልጹ መረጃዎች መንሰራፋታቸውን ተከትሎ የመብት ድርጅቶች ስጋታቸውን ሲገልፁ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች ፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ ስጋታቸውን ከገለጹት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ ምርጫውን የታዘቡት የአፍሪካ ህብረት ቡድን መሪው ክላሰው ኮሚሰሎም “የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ ነበር” ብለዋል::
የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን አባል የሆኑት ኦማን መሀማት በበኩላቸው አልፎ አልፎ የታዩና ሪፖርት የተደረጉ ችግሮች ቢኖሩም ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንደተጠናቀቀ ተናግረዋል፡፡
"እግዝአብሄርን እናመሰግናለን፤ ሁሉም ነገር በጥሩ ሁኔታ ተከናውኗል ፤ ያጋጠመ ችግር የለም፤ ዋናው ነገርም እሱ ነው፤ ሁሉም ነገር በእቅድ መሰረት ተሳክቷል" ብለዋል ኦማን መሀማት፡፡
በማእከላዊ አፍሪካዊቷ ሀገረ ቻድ በተካሄደው ምርጫ ሦስት ቀንደኛ ተቀናቃኞች ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸው የሚታወስ ነው፡፡
የሳልህ ኬብዞቦ ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ስድስት ተቀናቃኝ ኃይሎች በምርጫው ለመወዳደር እንደማይችሉ በሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መከልከላቸውም እንዲሁ የሚታወቅ ነው፡፡
ይህን ተከትሎ ታድያ ፕሬዝደንት ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ ለ6ኛ ጊዜ አሸንፈው ለሶስት አስርት አመታት የጨበጡትን በትረ ስለጣን ያስቀጥላሉ የሚለው የበርካቶች ግምት ሆኗል፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት የፀደቀው ሕገ-መንግስታዊ ህዝበ ውሳኔ እንደሚለው ከሆነ ፣ ፕሬዝደንት ዴቢ ከአሁን በኋላ በምርጫ እስከ ፈረንጆቹ 2033 ወይንም ለቀጣይ ሁለት የስልጣን ዘመናት ለመቆየት የሚያስችላቸው ሕጋዊ ማእቀፍ አላቸው፡፡