የቻድ ጦር በሰሜናዊ የሀገሪቱ ግዛት ካኔም የአማጺያን ተሽከርካሪዎችን ማውደሙን አስታውቋል
የቻድ አማጺያን ወደ ዋና ከተማዋ ኒጃሚና መጠጋታቸውን ተከትሎ በሀገሪቱ የሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ በጣም አስፈላጊ ያልሆኑ ሰራተኞችን ሀገሪቱን እንዲለቁ አዟል፡፡
አማጺያኑ ወደ ዋና ከተማው እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመሩት በቻድ የተካሄደውን ምርጫ ፕሬዘዳንት እድሪስ ደቢይ ለሶስተኛ ዙር የስልጣን ዘመን መምራት ከጀመሩ በኋላ ነው፡፡ በፈረንጆቹ 1990 ስልጣን የተቆናጠጡት ዴቢይ እስላማዊ ታጣቂዎችን በመዋጋት የፈረንሳይና የአሜሪካ ዋነኛ አጋር ናቸው፡፡
አማጺያኑ ወደ ዋና ከተማዋ ኒጃሚና በመቅረባቸውና የጸጥታ ችግር ይኖራል በሚል ስጋት ምክንያት፣ የአሜሪካ ኢምባሲ ሰራተኞች በመንገደኞች አውሮፕላን ቻድን እንዲለቁ መታዘዛቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የብሪታኒያ መንግስትም እንዲሁ የቻድ አማጺያንን የያዙ ሁለት ተሽከርካሪዎች ወደ ዋና ከተማዋ በመቃረባቸው ምክንያት ዜጎቹ ከሀገር እንዲወጡ አሳስቧል፡፡ ከባድ መሳሪያ የታጠቁ የቻድ የጸጥታ ሀይሎች በዋና ከተማዋ ሲዘዋወሩ እንደነበር ሮይተርስ የአይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
የቻድ ጦር በበኩሉ በሰሜናዊ የካኔም ግዛት የአማጺያን ተሽከርካሪ ማውደሙን አስታውቋል፡፡
ረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ ከቆዩት የአፍሪካ መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዴቢይ፣ በተለያየ ጊዜ የተቃጣበቸውን ጥቃት በስኬት ማክሸፍ ችለዋል፤ ይህን የሚያደርጉት አልፎ አልፎ በፈረንሳይ ድጋፍ ነበር፡፡