ታዋቂው የህንድ ተዋናይ አሚታብ ባቺቻን ቀረጻ ላይ እያለ ጉዳት ደረሰበት
የ80 አመቱ አሚታብ በሃይደራባድ ከተማ በቀጣይ አመት የሚወጣ ፊልም በመቀረጽ ላይ እያለ ነው ወድቆ የጎን አጥንቱ የተሰበረው
ከ200 በላይ የህንድ ፊልሞች ላይ የተወነው አሚታብ ባቺቻን በገጠመው ጉዳት የፊልሙ ቀረጻ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል ተብሏል
የህንድ ፊልም ሲነሳ ከብዙዎች አዕምሮ የማይጠፋው አሚታብ ባቺቻን አሁንም ተወዳጅ ትወናውን ማሳያቱን ቀጥሏል።
የ80 አመቱ ተዋናይ የእድሜው መግፋት ሳያግደው አድካሚ የፊልም ቀረጻዎችን እያደረገ ነው።
በትናንትናው እለት በደቡባዊ ህንድ ሃይደራባድ ከተማ “ፕሮጀክት ኬ” የተሰኘ የሳይንስ ልብወለድ ፊልም ሲቀረጽ ግን ያልጠበቀውን ጉዳት አስተናግዷል።
አሚታብ ትወና ላይ እያለ ወድቆ የጎን አጥንቱ ተሰብሯል፤ ከባድ ህመሙም ቀረጻውን አቋርጦ ወደ ሆስፒታል እንዲያመራ አድርጎታል።
ተወዳጁ ተዋናይ በሙምባይ ወደሚገኘው ቤቱ ከማምራቱ በፊት ከሃኪሞች ጋር መመካከሩንና ዘለግ ያለ እረፍት እንዲያደርግ መታዘዙን በግል ጦማሩ ላይ ማስፈሩንም ነው አሶሼትድ ፕረስ ያስነበበው።
በአደጋው ምክንያት በየቀኑ በቤቱ ዙሪያ የሚሰባሰቡ አድናቂዎቹን ማግኘት እንደማይችል አስታውቋል።
የደረሰበት ጉዳት እጅግ የከፋ ባይሆንም እረፍት ስለሚፈልግ የፊልሙ ቀረጻም እስከሚድን ድረስ መራዘሙ ተነግሯል።
ከ200 በላይ የህንድ ፊልሞች ላይ የተወነው አሚታብ፥ በፈረንጆቹ 1973 የሰራው “ዛንጀር” ወይንም “ዘ ቼይን” ፊልም እውቅናን አትርፎለት ከህንድ አልፎ በመላው አለም ተወዳጅ የሆኑ ፊልሞችን ለመስራት በቅቷል።
አድናቂዎቹ የጸጉር አቆራረጡን፣ አለባበስ እና አነጋገሩን ለማስመሰል የሚሸቀዳደሙለት ተዋናይ መሆንም ችሏል።
በፈረንጆቹ 1984 የፊልም ትወና ሙያውን ገታ አድርጎ ፖለቲካውን የተቀላቀለው አሚታብ ባቺቻን የፓርላማ ተወካይ ሆኖ ለሶስት አመት ከቆየ በኋላ ወደሚወደው ሙያ ተመልሷል።
በህንድ ፊልም ኢንዱስትሪ ላለፉት 50 አመታት በተወዳጅነት የሰራው አሚታብ የሚወደው ሙያ አደጋ ጥሎበታል።ከ200 በላይ የህንድ ፊልሞች ላይ የተወነው አሚታብ ባቺቻን በገጠመው ጉዳት የፊልሙ ቀረጻ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል ተብሏል