በቻይና ከሚገኙ 14 የአይፎን ማምረቻ ማዕከላት ውስጥ 5 በመቶው በ2023 ወደ ህንድ ይዛወራሉ
የአሜሪካው ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል ከቻይና ይልቅ ፊቱን ወደ ህንድ በማዞር የአይፎን ስልኮችን ምርት ለማሳደግ ማቀዱን የህንድ ንግድ ሚኒስትር ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ አፕል ከ5 አስከ 7 በመቶ የሚሆነውን ምርቱን የሚያመርተው በህንድ መሆኑን የገለጹት ሚነስትሩ፤ በቀጣይ የሚያመርተውን ምርት እስከ 25 ከመቶ ለማሳደግ አቅዶ እየሰራ ነው ማለታቸውም የህንድ ጋዜጣ " ቢዝነስ ቱዴይ" ዘግቧል፡፡
አፕል በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር ባይኖርም ፤ መረጃው ህንድ የአይፎን ምርቶችን በማምረት የቻይናን ሚና ልትቀማ መሆኑ አመላካች ነው ተብሏል፡፡
በዓለም ፋይናንሺያል አገልግሎቶች መፍትሄ ጠቋሚው የጄ.ፒ. ሞርጋን መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ደግሞ ከ14 የአይፎን ማምረቻ ማዕከላት 5 በመቶ የሚሆኑት በያዝነው አመት 2023 ወደ ህንድ የሚዛወሩ ይሆናል፡፡
እንደፈረንጆቹ በ2025 ኩባንያው 25 በመቶ የሚሆነውን ሁሉንም ዘመናዊ መሳሪያዎቹን ከቻይና ውጭ ለመስራት አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ጭምር ነው ያመላከተው፡፡
አሁን ላይ በአለም ዙሪያ ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙ የአይፎን ስልኮች፣ አይፓዶች እና ሌሎች ታዋቂ ምርቶች ቻይና በሚገኙ የአፕል ሰፋፊ የማምረቻ ማዕከላት የተመረቱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጅ ቻይና የ"ዜሮ-ኮቪድ" ፖሊሲን ተግባራዊ ማድረጓን ተከትሎ ከፍተኛ ፈተና የገጠመው አፕል ፊቱን ወደ ህንድ ለማዞር መገደዱ እየተነገረ ነው፡፡
የኮቪድ ስርጭትን ለመግታት በሚል በቤጂንግ ባለስልጣናት ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኘው ፖሊሲ በዜንግዡ ግዛት በሚገኘው የአይፎን ማምረቻ ማዕከል ላይ ተጽዕኖ ሳያሳድር እንዳልቀረም ነው ዘገባዎች ያመላከቱት፡፡
በዚህም አሁን ላይ የችርቻሮ መደብር ሰራተኞች መቅጠር የጀመረው አፕል በ 2023 የመጀመሪያ ሩብ አመት ውስጥ ዋና ዋና ማከማቻዎቹን በህንድ ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኑ ፋይናንሺያል ታይምስ ዘግቧል።
በህንድ የሚገኙት የአይፎን ሰሪዎች እንደ ፎክስኮን፣ ዊስትሮን እና ፔጋትሮን እንዲሁም እንደ ሱንዳ፣ አቫሪ፣ ፎክስሊንክ እና ሳልኮምብ ያሉ አቅራቢዎች ከነሃሴ 2021 ጀምሮ 150ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ የስራ እድሎች መፍጠር ችለዋል፡፡
እናም የአፕል ወደ ህንድ ትኩረት ማድረግ ከዚህ የበለጠ እደል ሊፈጥር እንደሚችል ነው የሚታመነው፡፡
ኩባንያው ከህንድ በተጨማሪ ምርቱን እስከ ቬትናም የማስፋፋት እቅድ እንዳለውም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡