ኮሮናን ሽሽት 3 ዓመት ሙሉ ቤቷን የዘጋችው ህንዳዊ “የቆሻሻ ክምር” ሊገድላት ሲቃረብ ተደርሶላታል
ጉሩግራም በተባለው አካባቢ ነዋሪ የሆነችው እናት “ልጄ ከቤት ከወጣ ኮሮና ይገድለዋል” የሚል ጭንቀቷ ለ36 ወራት ቤት አዘግቷታል
ባለቤቷ እና የልጇ አባትም የኮቪድ ክልከላ ሲላላ ለስራ ከወጣ በኋላ ተመልሶ እንዳይገባ ከልክላው ተከራይቶ ለመኖር መገደዱ ነው የተነገረው
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሰባት ዓመት ታዳጊ ልጅ ያላትን ህንዳዊ ክፉኛ ፈትኗታል።
የ36 ዓመቷ እናት “ልጄ ወደ ውጭ ከወጣ ይሞትብኛል” የሚል ጽኑ እምነት ስለነበራትም ያለፉትን ሶስት አመታት ከቤት አልወጣችም።
ስሟ ያልተጠቀሰው እንስት ከባድ የኮሮና ፍራቻ ያልተዋጠለት ባል ግን የኮሮና ክልከላዎች መላላት ሲጀምሩ ከቤቱ ይወጣል፤ ተመልሶ ወደ ቤቱ መግባት ግን አልተፈቀደለትም።
- በህንድ የልጅ ልጅ ሊያሳየን አልቻለም በሚል ልጃቸውን በ50 ሚሊየን ሩፒ የከሰሱ ወላጆች
- ህንድ የፍቅረኞች ቀን “ላሞችን በማቀፍ ቀን” እንዲተካ ያሳለፈችው ውሳኔ…
ኢንጂነሩ ሱጃን ማጅሂ ፥ ባለቤቱን ለማሳመን ለወራት ያደረገው ጥረት አልሳካ ሲል ቤት ተከራይቶ አዲስ ህይወት መምራት ግድ ሆነበት።ለራሱም ለሚስትና ልጁም የቤት ኪራይና የምግብ ወጪን መሸፈን ግን ከባድ እየሆነበት ሄደ።
የሚስቱ እና የልጁ ናፍቆትም ከቁጥጥሩ ውጭ እየሆነ ሲመጣ ማጅሂ ባለፈው ሳምንት ወደ ፖሊስ ጣቢያ በማምራት ቅሬታውን አቅርቧል ይላል ኦዲቲ ሴንትራል በዘገባው።
የጉሩግራም ከተማ ፖሊሶችም ማጅሂ ያቀረበውን አቤቱታ ሲስሙ ለማመን ተቸግረው የነበረ ቢሆንም፥ ባለቤቱን በስልክ ሲያነጋግሯት እውነት መሆኑን ነግራቸዋለች።
ኮቪድ ሲጀምር 7 አመት እድሜ የነበረው ታዳጊ ልጃቸው አሁን 10 አመት ሆኖታል፤ ጸጉሩም የሚቆርጠው ጠፍቶ የሴቶችን የሚያስንቅ ሆኖ ረዝሟል ብሏል የማጅሂን አቤቱታ እየተከታተለ የሚገኘው ፖሊስ።
ፖሊሱ የልጁን ደህንነት በቪዲዮ እንድታሳየው ጠይቋት ያሉበትንም ቤት እየተዟዟረች ስታሳየውም በቆሻሻ ክምር መሞላቱን ተመልክቻለሁ ብሏል።
አሁንም ድረስ “ልጄ ከቤቱ ከወጣ በኮሮና ይሞትብኛል” ብላ የምታምነው እንስት የባለሙያ ምክር እንደሚያሻት ተገልጿል።
የምርመራ ፖሊሲ አሳምኗት ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤቷ ወጥታ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ያመራችው ህንዳዊት እናት፥ ወደ ሆስፒታል ተወስዳ ህክምናዋን እየተከታተለች ነው ተብሏል።
ፖሊስ ሶስት አመት ሙሉ ከውጭ ግንኙነት የተገለለውን ቤተሰብ ቤት ሰብሮ ሲገባ ፥ በየአቅጣጫው የቆሻሻ ክምር ተቆልሎ ተግኝቷል።
እናት ከኮቪድ አተርፈዋለሁ ያለችውን ልጅ በቆሻሻ ልትገድለው ነበር ብለዋል ፖሊሶች።