የእርዳታ ምግብ የጫኑ 500 ተሽከርካሪዎች ትግራይ መድረሳቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገለፀ
የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ በኋላ ከትግራይ ክልል የቆዳ ስፋት ውስጥ በ14 በመቶው ብቻ ድጋፍ እንደሚያደርግ በቅርቡ አስታውቋል
የድርጅቱን እርዳታ ምግብ የጫኑ ተሽከርካሪዎቹ ከሱዳን ነው ወደ ትግራይ የገቡት
አስቸኳይ የእርዳታ ምግብ የጫኑ 500 ተሽከርካሪዎች ትግራይ መድረሳቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ፡፡ የእርዳታ ምግቡን የጫኑ ተሽከርካሪዎቹ ከሱዳን ነው ወደ ትግራይ የገቡት፡፡
በክልሉ በተደረገው ውጊያ ለተጎዱ 2.1 ሚሊዬን ዜጎች የምግብ እርዳታዎችን ለማድረግ በማሰብ እየሰራ መሆኑን ያስታወቀው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ፣ ሌሎች ተጨማሪ 500 የእርዳታ ምግቦችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ ለመግባት በጉዞ ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡
ድንበር ዘለሉን ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ላሳየው ትብብር የሱዳን መንግስትን ያመሰገነው የፕሮግራሙ የሱዳን ማስተባበሪያ እስካሁን ከ20 ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ ለማቅረብ መቻሉንና ተጨማሪ 25 ሺ ሜትሪክ ቶን የእርዳታ ምግብ በመጓጓዝ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የምግብ እርዳታው አስቸኳይ ድጋፍን ለሚፈልጉ ዜጎች የሚውል ነው፡፡
4.5 ሚሊዮኝ የሚደርሱ የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን ጨምሮ ከ16 ሚሊዮን በላይ ህዝቦቿ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያ ፣ የተባበሩት መንግስታት ለዘርፉ የሚውል 65 ሚሊዮን ዶላር መልቀቁም ተገልጿል፡፡
ይሁን እንጂ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ተጨማሪ ፈንድ እና ሰላማዊ እና ያልተገደበ ተደራሽነት እንደሚያስፈልጋቸውም ነው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ያስታወቀው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ በሰጠው መግለጫ ፣ ከዚህ በኋላ ከትግራይ ክልል አጠቃላይ የቆዳ ስፋት ውስጥ በ14 በመቶው ብቻ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
ቀሪው 86 በመቶ የዓለም ምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ በሌሎች ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጭ ተቋማት እንደሚሸፈን ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በወቅቱ ገልጸዋል፡፡
እስካሁን በክልሉ በመደረግ ላይ ካለው ሰብዓዊ ድጋፍ 70 በመቶ የሚሆነው በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው መባሉ የሚታወስ ነው፡፡